ዲላ ዩኒቨርስቲ የ1 ሚሊዮን 200ሺህ ብር ግምት ያለው የምግብና ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
ዲላ ዩኒቨርስቲ የ1 ሚሊዮን 200ሺህ ብር ግምት ያለው የምግብና ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ
ዲላ፤ ሚያዚያ 21/2012(ኢዜአ) ዲላ ዩኒቨርሲቲ በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ለችግር ለተጋለጡ ወገኖች የ1 ሚሊዮን 200ሺህ ብር ግምት ያለው የምግብና የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ።
በሌላ በኩል በጌዲኦ ዞን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን በሚጥሱ አካላት ላይ የሚወሰደው እርምጃ ተጠናክሮ መቀጠሉም ተገልጿል።
የዲላ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ችሮታው አየለ ድጋፉን ዛሬ ለጌዴኦ ዞን የኮሮና መከላከል ግብረ ኃይል ባስረከቡበት ወቅት እንዳሉት ከድጋፉ ውስጥ 750 ሊትር የምግብ ዘይትና 27 ሺህ 750 ኪሎ ግራም ጤፍ፣ ሩዝ፣ ፓስታ፣ ሽሮና በርበሬ ይገኙበታል።
እንዲሁም 3 ሺህ 500 ሊትር የንጽህና መጠበቂያ ፈሳሽ ሳሙናና ሳኒታይዘር መስጠታቸውንም ተናግረዋል።
ዩኒቨርስቲው ወረርሽኙን ለመግታት የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ ከ7 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት መድቦ እየሰራ መሆኑን ያመለከቱት ዶክተር ችሮታው ድጋፉም የዚሁ እንቅስቃሴ አካል መሆኑን ገልጸዋል።
የኮሮና ቫይረስ ስርጭት የሚያደርሰውን ጫና ለመቋቋም የተለያዩ የእህል መጋዘኖችን በማዘጋጀት ሃብት የማሰባሰብ ስራ በስፋት እየተከናወነ መሆኑን የተናገሩት ዩኒቨርሲቲው ያደረገውን ድጋፍ የተረከቡት የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪና የኮሮና መከላከል ግብረ ኃይል ሰብሳቢ አቶ ገዙ አሰፋ ናቸው።
የዲላ ዩኒቨርሲቲ የህብረተሰቡን ግንዛቤ ከማሳደግ ጎን ለጎን በቫይረሱ ሳቢያ ጉዳት ለሚደርስባቸው ዜጎች ያደረገው ድጋፍ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን በመግለጽ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
በሌላ በኩል በጌዲኦ ዞን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን በሚጥሱ አካላት ላይ የሚወሰደው እርምጃ ተጠናክሮ መቀጠሉን በዞኑ የኮሮና መከላከል ግብረ ኃይል አመለከተ።
የግብረ ኃይሉ አባልና የዞኑ ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ወርቅነህ ጋሹ ዛሬ እንደገለጹት እስካሁን በዞኑ ስምንት ወረዳዎችና አራት ከተሞች ምርት የደበቁና ዋጋ ጨምረው ሲሸጡ የተገኙ 4 ሺህ 314 የንግድ ድርጅቶች ላይ እርምጃ ተወስዷል።
እርምጃውም የገንዘብ ቅጣት ፣ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያና በአራት ድርጅቶች ላይ ደግሞ ክስ መመስረቱን ጠቅሰዋል።
ለቫይረሱ መስፋፋት መንስኤ ይሆናሉ ተብለው የተገመቱ አንድ ሺህ 900 የጫት መሸጫና ሺሻ ቤቶች እንዲታሸጉ ተደርጓል ብለዋል።
የዞኑ መንገድና ትራንስፖርት መምሪያ ምክትል ኃላፊና የግብረ ኃይሉ አባል አቶ ረድኤት ክፍሌ በበኩላቸው ባለፈው አንድ ሳምንት ብቻ የአዋጁን ደንጋጌዎች ተላልፈው የተገኙ 88 አሽከርካሪዎች 88ሺህ ብር መቀጣታቸውን ገልጸዋል።
እነዚህ የህዝብ ማመላለሻ፣የጭነት እና የሞተር ብስክሌት አሽከርካሪዎች በገንዘብ የተቀጡት ከተፈቀደ ጭነት ልክ በላይ በመጫናቸው ነው።
በሁሉም ዘርፎች ህግን ተላልፈው በሚገኙ አካላት ላይ የሚወሰዱ እርምጃዎች ተጠናክሮ መቀጠሉንም የግብረ ኃይሉ አባላት አመልክተዋል።