ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ከስደት የተመለሱ ዜጎቿን እየረዳች ነው

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 21/2012( ኢዜአ) ኢትዮጵያ በመካከለኛው ምሥራቅና በጎረቤት አገሮች በስደት የነበሩ 9ሺህ 400 ዜጎቿን ተቀብላ እያስተናገደች መሆኗን ዓለም አቀፍ የስደተኞች ድርጅት ገለጸ።

ኢትዮጵያ ለኮሮና ወረርሽኝ በተዘጋጁ ለይቶ ማቆያ ጣቢያዎች እንክብካቤ እየተደረገላቸው ያሉት በዋነኝነት ከሳዑዲ ዓረቢያ፣ከጅቡቲ፣ከሶማሊያና ከሱዳን የተመለሱ ዜጎች ናቸው።

ለተመላሾቹ ድርጅቱ  ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በመተባበር በማቆያ ጣቢያዎቹ የምግብና የሕክምና አገልግሎት እየተሰጣቸው ነው።

ተመላኞቹ በጣቢያዎቹ የሚኖራቸውን ቆይታ ሲያጠናቅቁ ወደ መኖሪያ ቀዬአቸው የሚመለሱበት ድጋፍ እንደሚደረግላቸውም ድርጅቱ አስታውቋል።

ለዚህም ከክልል መንግሥታት፣ከሠራተኛ ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዲሁም ከሴቶች፣ሕጻናትና ወጣቶች ሚኒስቴሮች በትብብር እንደሚሰራ አመልክቷል።

የሠራተኛ ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጌጎ ተስፋዬና የድርጅቱ የኢትዮጵያ ተወካይ ማውሪን አቼንግ ስድስት ኪሎ የሚገኘውን የማቆያ ጣቢያ መጎብኘታቸውንም ገልጿል።

ድርጅቱ በማቆያ ጣቢያዎቹ ለሚገኙ ተመላሾች ወረርሽኙን ለመከላከል የሚረዱ የመኝታ አልባሳት፣ሳሙና የእጅ ንጽህና መጠበቂያ(ሳኒታይዘር) ድጋፍ ማድረጉን አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም