ኮሚሽኑ የሙቀት መለኪያ መሣሪያዎች ድጋፍ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
ኮሚሽኑ የሙቀት መለኪያ መሣሪያዎች ድጋፍ አደረገ
ድሬዳዋ ሚያዝያ 21/2012( ኢዜአ) የድሬዳዋ አስተዳደር ስፖርት ኮሚሽን የኮሮና ቫይረስ ስርጭት ለመከላከል የሚያግዙ 300ሺህ ብር በሆነ ወጪ የገዛቸው የሙቀት መለኪያ መሣሪያዎችን ለጤና ቢሮ አስረከበ።
ድጋፉን ያስረከቡት የአስተዳደሩ ስፖርት ኮሚሽነር ሻኩር አህመድ እንዳሉት ለቢሮው ያስረከቧቸው 46 የሙቀት መለኪያ/ ቴርሞ ስካን/ መሣሪያዎች ናቸው።
መሣሪያዎቹ በጤና ባለሙያዎች ተመርምረው የተረጋገጡ መሆናቸውን ጠቁመው "ኮሮና ቫይረስ ስርጭት ለመከላከልና የቫይረሱ አንዱ ምልክት የሆነውን የሙቀት መጠን ለመመርመር ያግዛል" ብለዋል፡፡
በተለይ ህዝብ በብዛት በሚገለገልባቸው ተቋማትና የህክምና ማዕከላት መግቢያ ላይ መሣሪያዎቹ ጥቅም ላይ ሊውሉ እንደሚችሉ አመልክተዋል፡፡
በተጨማሪም በ150 ሺህ ብር የተገዙ የዳቦ ዱቄትና ማካሮኒ ለአስተዳደሩ የኮሮና መከላከል ግብረ ኃይል ሀብት አሰባሳቢ ኮሚቴ ማስረከባቸውን ተናግረዋል፡፡
ባለፈው ሣምንትም ከ1 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ በጀት የተገዙ የተለያዩ የምግብ ዓይነቶች ለኮሚቴው መስጠታቸውንም አስታውሰዋል ፡፡
የሙቀት መለኪያ መሳሪያዎችን የተረከቡት የድሬዳዋ አስተዳደር ጤና ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ለምለም በዛብህ በበኩላቸው ቫይረሱ ለመከላከል በሚደረገው እንቅስቃሴ ውስጥ ኮሚሽኑ እያበረከተ የሚገኘው አስተዋጽኦ በአርአያነት የሚጠቀስና የሚያስመሰግነው ነው ብለዋል፡፡
ድጋፉ ወቅታዊና ጤና ቢሮው ያለበትን እጥረት ለማሟላት እንደሚያግዝ ጠቅሰው መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማትም ሆነ ባለሃብቱ የሚያደርጉትን ድጋፍ እንዲያጠናክሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡