በአማራ ክልል 171 ሺህ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች የኮሮና ቫይረስ በመከላከል ስራ ተሰማርተዋል - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል 171 ሺህ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች የኮሮና ቫይረስ በመከላከል ስራ ተሰማርተዋል
ባህርዳር-ሚያዚያ 21/2012 በአማራ ክልል 171 ሺህ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶችን በማሳተፍ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል እየሰራ መሆኑን የክልሉ ሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ገዳይ ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው ምክትል ሃላፊና የኮሮና ቫይረስ መከላከል ግብረ ኃይል አባል አቶ አባይነህ ጥላሁን ዛሬ በሰጡት መግለጫ ቢሮው በክልሉ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ከተቋቋመው ግብረ ሃይል ጋር በቅንጅት እየሰራ ይገኛል።
በቢሮው የሚመራ ንኡስ ግብረ-ሃይል በማቋቋም በየአካባቢው የሚገኙ ወጣቶችን በበጎ ፈቃድ ስራ በማሰማራት በሽታውን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚደረገውን ጥረት እንዲያግዙ እየተደረገ ነው።
ለህብረተሰቡ ግንዛቤ በመፍጠር፣ መከላከያና መተላለፊያ መንገዶችን በማስተማር፣ ሀብት በማሰባሰብ፣ አቅመ ደካሞችን በማገዝ፣ የተቸገሩትን በመርዳትና በሌሎችም ተግባራት ተሰማርተው እየሰሩ ነው ብለዋል ።
ወጣቶቹ ባሰባሰቡት ገንዘብም ረዳት ለሌላቸው አረጋዊያንና ህጻናት ምግብና አልባሳት ማቅረባቸውን ጠቁመው በማረሚያ ቤቶች ለሚገኙ ሴቶችና ህጻናት በ500 ሺህ ብር ወጪ የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶችን አድለዋል።
በተጨማሪም ከቢሮው ጋር በመተባበር ዛሬ ከ300 ሺህ ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸው ሳኒታይዘር፣ ሳሙና፣ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭንብልና ሌሎች የመከላከያ ቁሳቁሶች ለሁሉም ዞኖችና የከተማ አስተዳደሮች እንዲሰራጭ አድርገዋል።
የክልሉ በጎ ፍቃደኛ ወጣቶች ራሳቸውን ከኮሮና ቫይረስ በመጠበቅ እያበረከቱት ያለው አስተዋጽኦ አበረታች በመሆኑ በጎ ተግባራቸው ተጠናክሮ እንዲቀጥል መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።
የአማራ ክልል ወጣቶች ማህበር ሊቀመንበር ወጣት አባይነህ ጌጡ በበኩሉ ወጣቶቹ በህብረተሰቡ ላይ ኮሮና ቫይረስ ሊያደርስ የሚችለውን ችግር ለመቅረፍ በቁርጠኝነት የመሪነት ሚና እየተወጡ ነው ብሏል ።
በጎ ፈቃደኛ ወጣቶቹ ጉልበታቸውንና እውቀታቸውን በመጠቀምና ከኪሳቸው ያላቸውን በማዋጣትጭምር በሽታውን ለመግታት በሚደረገው ጥረት ግንባር ቀደም ተዋናይ ሆነው በመንቀሳቀስ ላይ እንደሚገኙ አስረድቷል ።