ቀጥታ፡

የንፅህና መጠበቂያ ምርቶች ለህብረተሰቡ በአቅራቢያው ተደራሽ እንዲሆን እየተሰራ ነው

ሚያዚያ 21/2012 (ኢዜአ) ለኮሮና ቫይረስ ቅድመ ጥንቃቄ  የሚያገለግሉ የንፅህና መጠበቂያ ምርቶች ላይ የሚስተዋለውን ህገወጥ ተግባራት በመከላከል  ለህብረተሰቡን በአግባቡ እንዲቀርብ እየተሰራ መሆኑን  የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ገለፀ፡፡

የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ መስፍን አሰፋ ለኢዜአ እንደገለጹት በከተማ ው የተቋቋመው ግብር ሃይል ከኮሮና ስጋት ጋር ተያይዞ ከንፅህና መጠበቂያ በተጨማሪ በአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች ላይ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ ባደርጉና በደበቁ ከ54 ሺህ የሚበልጡ የንግድ ተቋማት ላይ  በእለታዊ ተግባራቸው ላይ ክትትል ተደርጓል ፡፡

ከነዚህም ከ4 ሺህ በላይ በሚሆኑት ላይ አስተዳደራዊ እርምጃ   መወሰዱን ገልጸው፤ 2 ሺህ 500 በሚሆኑት ላይ ከጠፋታቸው እንዲታረሙ ተጨማሪ የግዴታ ውል ገብተው ወደ ስራ መመለሳቸውን  ተናግረዋል፡፡

እንደሃላፊው ገለጻ ጉዳያቸው   በህግ አግባብ  መታየት ያለበት   የንግድ ተቋማት  ለህግ  ቀርቡው በሂደት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

የኮሮና ቫይረስ ስርጭት ለመግታት የህብረተሰቡ ፍላጎት በሚመጥን መልኩ የከተማ አስተዳደሩ የንፅህና መጠበቅያ አልኮልና የሳንታይዘር ምርቶችን  በከነማ ፋርማሲዎች በኩል  ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ የተሞከረ ቢሆንም መጨናነቅ አጋጥሞ እደነበር  አስታውሰዋል፡፡

ይሄንን ችግር ለመቅረፍም የንጽህና መጠበቅያ ምርቶች በየወረዳው ባሉ  የሸማች ህብረት ስራ ማህበራት በኩል  እንዲቀርብ መደረጉን  ምክትል ሃላፊ  ተናግረዋል፡፡

በየጊዜው የህገወጥ ድርጊቶች  አካሄዱን እየቀያየረ እንደሚገኝ  የጠቆሙት ምክትል ሃላፊው፤ ይህንን ለመከላከል  የቁጥጥር ስርአቱን  በማጥበቅ  በርካታ ስራዎች እየተሰሩ እንደሚገኙ ነው ያነሱት፡፡

ለአብነትም በንፅህና መጠበቅያ ምርቶችን ላይ  ባእድ ነገሮችን  በግብአትነት ተጠቅሞ  በማዘጋጀት ለገበያ ሲያቀርቡ የነበሩ ግለሰቦችን የተቋቋመው ግብረ ሃይል ከሰላምና ፀጥታ አካላት ጋር  በመሆን እርምጃ መውሰዱን ነው ምክትል ቢሮ ሃላፊው ያብራሩት፡፡

በአገር አቀፍ ደረጃ  የወጡ የጥራት ደረጃዎችን ያላሟሉ ምርቶ ገበያ ላይ እንዳይቀርቡ ክትትል በማድረግና ከተገኙም ህጋዊ እርምጃ በመውሰድ ለማስተካከል እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

የንጽህና መጠበቂያ ምርቶችን አቅርቦትን ለማሳደግ በተደረገው እንቅስቃሴ በሀገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎች ከ3 ሚሊዮን ሊትር በላይ ሳኒታይዘር ለገበያ መቅረቡን አቶ መስፍን ተናግረዋል።

በሌላ በኩል በሀገሪቱ የሚገኙ 43 የጠጣርና ፈሳሽ ሳሙና አምራች ኢንዱስትሪዎች  አቅምን በማሳደግ በቀን 2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ኪሎ ግራም ሳሙናና 358 ሺህ ሊትር የሚጠጋ ፈሳሽ ሳሙና እየተመረተ እንደሚገኝ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ገልጿል፡፡

በቀጣይም በቀን 3 ሚሊዮን ኪሎ ግራም ሳሙናና 744 ሺህ 873 ሊትር ፈሳሽ ሳሙና ለማምረት እየተሰራ መሆኑም   ተጠቅሷል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም