ቀጥታ፡

በትግራይ ኮሮናን ከመከላከሉ በተጓዳኝ ለመኸሩ ወቅት የእርሻ ዝግጅት እየተደረገ ነው

መቀሌ (ኢዜአ) ሚያዝያ 21/12 ዓ/ም በትግራይ ክልል የኮሮና ቫይረስን ከመከላከሉ በተጓዳኝ በመጪው የመኸር ወቅት ከ1 ሚሊዮን 300ሺህ በላይ ሄክታር መሬት ለማልማት ዝግጀት እየተደረገ መሆኑን የክልሉ ግብርናና ገጠር ልማት ቢሮ አስታወቀ። 

የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ አሰፋ ሕድጎት ለኢዜአ እንደገለጹት ለምርት ዘመኑ እየተደረገ ያለው ዝግጅት  በክልሉ ውስጥ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል ግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ  ነው፤

በዚህም የአርሶ አደሮች ስልጠና፣የእርሻ ግብአቶት ስርጭት እና ተጓዳኝ መሰናዶዎች በመካሄድ ላይ ይገኛል።

የአርሶ አደሮች ስልጠና ካለፈው መጋቢት ወር ጀምሮ በክልሉ ዞኖችና ወረዳዎች እየተሰጠ መሆኑን ያመለከቱት  አቶ አሰፋ መሃል ላይ የኮሮና ቫይረስ መከሰትን ተከትሎ አንድ ላይ በመሰብሰብ ሲካሄድ የቆየውን ስልጠና ተቀይሮ በሌላ መልኩ እንዲሆን መደረጉን  ተናግረዋል።

''የስልጠና አካሄዳችን ቀይረን አካሂዱን ከልሰን ቴክኖሎጂዎች በመጠቀም በቪዲዮና የሬድዮ ፕሮግራም አድርገን ከወረዳ እስከ ቀበሌ ያሉት ባለሙያዎች ጥብቅ ክትትል የሚያደርጉበት ነው''ብለዋል።

የልማት ቡድኖችና ኔትዎርኮችን በመጠቀም አርሶ አደሮች ተጨማሪ ድጋፍ የሚያገኙበት ሁኔታ እየተመቻቸ መሆኑንም ገልጸዋል።

የቢሮው ምክትል ኃላፊው እንዳሉት የክልሉ አርሶ አደሮች የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን በመከላከል መደበኛ የእርሻ ስራቸውን እንዲያከናውኑ አልኮል፣ ሳኒታይዘር እና ሌሎች ግብአቶች እየተሰራጩ ነው።

ለእርሻው ስራው በግብአትነት የሚገለግል  በወረዳዎች እና ቀበሌዎች በኩል 300 ሺህ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ እየተሰራጨ መሆኑን   አቶ አሰፋ  ገልጸዋል።

 ምርጥ ዘርም  ወደ አርሶ አደሮች ለማዳረስ እስካሁን 11 ሺህ ኩንታል ዘር የማጣራት ስራ ተሰርቶ ተዘጋጅቷል፤ አንበጣን አስቀድሞ ለመከላከል እስከ ቀበሌ ድረስ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ክትትል እያደረገን ነው ብለዋል።

በትግራይ ምስራቃዊ ዞን እንደርታ ወረዳ የእንዳማሪያም ድሐን ቀበሌ አርሶ አደር ገብረስላሴ ሃብቱ በሰጡት አስተያየት የኮሮና ቫይረስን  ለመከላከል እጃቸውን እየታጠቡ ጥንቃቄ ከማድጉ በተጓዳኝ  መደበኛ የእርሻ ስራቸው መጀመራቸውን ተናግረዋል።

" ያለኝን ማሳ  በበሬ  እያረስኩና እያለሰለስኩ እገኛለው ያሉት አርሶ አደሩ ለመኸር ወቅት የሚያገላግላቸው ማዳበሪያ እና ምርጥ ዘር ለመግዛት በወረዳቸው ተመዝግበው እየጠበቁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

"መደበኛ የእርሻ ስራችን ከወትሮ በተለየ ሁኔታ አካላዊ ርቀታችንን ጠብቀን እየሰራን ነው፤ ስንጓዝም ርቀታችንን ጠብቅን ነው" ያሉት ደግሞ የዚሁ ቀበሌ አርሶ አደር ቄስ እያሱ ረዳ ናቸው።

በደቡባዊ ምስራቅ የህንጣሎ ወረዳ አርሶ አደር ዕቋር ሓዱሽ በበኩላቸው፣ለመደበኛ የመኸር እርሻ ዝግጅት እያደረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት  ማሳቸው በማረስና በማለሳለስ ላይ እንደሚገኙ አመልክተው  በግብአትነትም በረዳቸው እየተከፋፈለ ካለው ሦስት ኩንታል ማዳበሪያ መግዛታቸውን ገልጸዋል።

የምርጥ ዘር ጥያቄ አቅርበው በመመዝገብ  ምላሽ በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኙም አመልክተዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም