የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ለመከላከል የወጣው የሥራ ቦታ ፕሮቶኮል እንዲተገበር ተጠየቀ - ኢዜአ አማርኛ
የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ለመከላከል የወጣው የሥራ ቦታ ፕሮቶኮል እንዲተገበር ተጠየቀ
አዲስ አበባ ሚያዝያ 21/2012 (ኢዜአ) የኮቪድ 19 ዓለም አቀፍ ወረርሽኝን ለመከላከልና ምላሽ ለመስጠት የተዘጋጀው የሥራ ቦታ ፕሮቶኮል ተግባራዊነቱ እንዲጠናከር ተጠየቀ።
የኮሮና ወረርሽኝ የዓለም ስጋት መሆኑን ተከትሎ ቫይረሱን ለመከላከል የሥራ ቦታ ምላሽ ፕሮቶኮል በሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እየተተገበረ ይገኛል።
ፕሮቶኮሉ በመንግሥት፣ በአሠሪና በሠራተኛው መካከል ተግባራዊ የሚደረግ ሲሆን፤የኮሮ ቫይረስ ወረርሽኝ በአገሪቱ ኢኮኖሚው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩ ሲረጋገጥ ታሳቢ ሁኔታዎች ላይ በመመስረት ተፈጻሚ ይሆናል።
በተጨማሪም በድርጅቶች ቀጣይነትና ህልውና፣ በሠራተኞች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ላይ የሚፈጥረውን ጉዳት ለመቀነስ ያግዛል ተብሎም ታምኖበታል።
እንዲሁም በመሠረታዊ የሥራ ቦታ የቫይረሱ መከላከያ ስልቶችና አሰሪና ሠራተኛን በተመለከተ በየደረጃው የሚወሰዱ ሕጋዊና አስተዳደራዊ እርምጃዎች ሥር አሰሪና ሠራተኞች እንዲሁም የደህንነት ኮሚቴዎች የሚወስዷቸው ጥንቃቄዎችን ያካትታል።
በርካታ አሰሪዎችና ሠራተኞች የሥራ ቦታ ፕሮቶኮሉን ተቀብለው ተግባራዊ እያደረጉ ቢሆንም፤ አንዳንድ ተቋማት ግን ከዚህ በተቃራኒ ተግባራዊነቱን እንዳላከበሩ የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማህበራት ኮንፌደሬሽን (ኢሠማኮ)ፕሬዚዳንት አቶ ካሳሁን ፎሎ ተናግረዋል።
ይልቁንም ተቋማት አጋጣሚውን በመጠቀም ሠራተኞቻቸውን በዲሲፕሊን ምክንያትና ሰበብ ከሥራ የሚያሰናብቱበት ሁኔታ ይስተዋላል ብለዋል።
በመሆኑም በፕሮቶኮሉ መሠረት እንዲተገበርና እየተስተዋሉ ያሉት ክፍተቶችም እንዲታረሙ ፕሬዚዳንቱ ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ አሰሪዎች ኮንፌደሬሽን ፀሐፊ ዳዊት ሞገስ በበኩላቸው ኢንዱስትሪውም ሆነ አሰሪው ወረርሽኙ ከመከሰቱ አስቀድሞም ቢሆን ከችግር እንዳልወጡ ገልጸዋል።በተለይ የውጭ ምንዛሪ እጥረት የጎላ እንደነበር በማመልከት።
ወቅቱ እርስ በርስ መተጋገዝ እንደሚጠይቅ በማመን አሰሪዎች ለሠራተኞቻቸው ከአንጡራ ሃብታቸው ደሞዝ እየከፈሉ ናቸው ብለዋል።
ፕሮቶኮሉን ያልተገበሩ ተቋማት ሁኔታውን ባለመረዳት ካልሆነ በስተቀር ሠራተኞቻቸውን ለመበተን እንደደማይፈልጉ አቶ ዳዊት ተናግረዋል።
የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ በበኩላቸው ከፌዴራል እስከ ክልል ወጥ ለሆነው ፕሮቶኮል አሰራር መዘርጋቱንና ተግባራዊነቱም እየተገመገመ መሆኑን ገልጸዋል።
በፕሮቶኮሉ አሰራርና አተገባበር ሂደት ላይ ውይይት እየተደረገና ምላሽ በመሰጠት ላይ እንደሚገኝ ያስረዱት ሚኒስትሯ፣ ከዚህ ባለፈ ለሕግ ተገዥ ያልሆነ አካል ከተገኘ እንዳስፈላጊነቱ እርምጃ ይወሰድበታል ብለዋል።
የዓለም የሙያ ደህነነትና ጤንነት ቀን በኢትዮጵያ ለ15ኛ በዓለም አቀፍ ደረጃ ደግሞ ለ16ኛ ጊዜ "ወረርሽኙን እንግታ፤ የሥራ ቦታ ደህንነትና ጤንነት ህይወትን ይታደጋል!'' በሚል መሪ ሃሳብ ተከብሯል ።
የሠራተኛና ማህራዊ ጉዳይ ሚኒስትሯን ጨምሮ ሌሎችም የሥራ ኃላፊዎች ደም ለግሠዋል።