የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባውን ነገ ያካሂዳል - ኢዜአ አማርኛ
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባውን ነገ ያካሂዳል
አዲስ አበባ ሚያዝያ 21/2012 (ኢዜአ) የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነገ በሚያካሂደው 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 15ኛ መደበኛ ስብሰባ የተለያዩ ውሳኔዎችን መርምሮ እንደሚያጸድቅ ይጠበቃል።
ምክር ቤቱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጠቅላላ ምርጫን በተመለከተ ያቀረበውን የውሳኔ ሐሳብ ጨምሮ ሌሎች አምስት አጀንዳዎችን የሚመለከት ይሆናል።
ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የጠቅላላ ምርጫን በተመለከተ ያቀረበውን የውሳኔ ሃሳብ ምርምሮ ያፀድቃል፤ የቀጣይ የመፍትሄ ሃሳብ እንዲቀርብም ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ ይመራል ተብሎ ይጠበቃል።
በኢትዮጵያና በሳዑዲ የልማት ፈንድ መካከል ለሁለተኛው ሀገር አቀፍ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት፣ ሳኒቴሽንና ሃይጂን ፕሮግራም ማስፈጸሚያ የተደረገው የብድር ስምምነት ረቂቅ አዋጅም ውይይት ተደርጎበት እንደሚፀድቅ ይጠበቃል።
ኢትዮጵያ ከኮሪያ ኤክስፖርት-ኢምፖርት ባንክ ጋር ለአዳማ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የልህቀት ማዕከል መመስረቻ፤ ከሳዑዲ የልማት ፈንድ ለደብረ ማርቆስ-ሞጣ የመንገድ ሥራ ማሻሻያና ማሳደጊያ ፕሮጀክት፤ ከዓለም አቀፍ የግብርና ልማት ፈንድ ለቆላማ አካባቢዎች የኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ የተደረገውን የብድር ስምምነት ለማጽደቅ የቀረበ ረቂቅ አዋጅ መርምሮ እንደሚያጸድቅም ይጠበቃል።
ከዚህም በተጨማሪ ምክር ቤቱ የኤሌክትሮኒክ ትራንዛክሽንን ለመደንገግ የቀረበ ረቂቅ አዋጅ መርምሮ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ የሚመራ መሆኑ ተመልክቷል።
የምክር ቤቱን 5ኛ ዓመት የስራ ዘመን 14ኛ መደበኛ እና 2ኛ ልዩ ስብሰባ ቃለጉባኤዎችን መርምሮ ማጽደቅ ቀዳሚ አጀንዳው እንደሆነም ምክር ቤቱ ለኢዜአ የላከው መግለጫ ያመለክታል።