ቀጥታ፡

በወለጋ ዩኒቨርሲቲ የኮሮና ቫይረስ ምርመራ ማእከል ለአገልግሎት ዝግጁ ሆነ

ነቀምቴ (ኢዜአ) ሚያዝያ 21/2012 የወለጋ ዩኒቨርሲቲ ሪፌራል ሆስፒታል ከኮሮና ቫይረስ ጋር ተያይዞ በቀን 500 ናሙናዎች የመመርመር አቅም ያለው ማእከል ከትናንት ጀምሮ ለአገልግሎት ዝግጁ ማድረጉን ገለፀ ። 
የሪፈራል ሆስፒታሉ ሥራ አስኪያጅና የፅንስና የማሕፀን ስፔሻሊስት ዶክተር ተመስገን ጥላሁን እንደገለፁት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልልን ጨምሮ ለምዕራብ ኦሮሚያ ዞኖች አገልግሎት የሚሰጥ የኮቪድ 19 መመርመሪያ ማዕከል ከትናንት ጀምሮ አገልግሎት ለመስጠት ዝግጁ ሆኗል ።

"ማእከሉ የኢንፌክሽን መከላከያ፣ ለታማሚዎች ህክምናና የሥነ ልቦና አገልግሎት ይሰጣል" ያሉት ዶክተር ተመስገን በቂ የሰው ኃይል የተሟላለትና በቀን እስከ 500 ሰዎችን የመመርመር አቅም ያለው ነው ብለዋል ።

የሆስፒታሉ ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር አሰፋ ነገሪ በበኩላቸው ማእከሉ 5 ሜካኒካል ቬንትሌተሮችና በኦክስጂን ፕላንት ጭምር የተደረጃና አስፈላጊው ግብአቶች የተሟሉለት መሆኑን ገልፀዋል ።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ሐሰን ዩሱፍ እንዳሉት ደግሞ ዩኒቨርሲቲው ግንዛቤ ለመፍጠር በምሥራቅ ፣ በምዕራብና በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞኖች ብዙ ሥራ መስራቱንና በነቀምቴ ዋና ጊቢ፣ በግምቢና በሻምቡ ካምፓሶች የለይቶ ማቆያ ማእከላት አዘጋጅቷል ።

የምርመራ ማዕከሉ በምዕራቡ የአገሪቱ ክፍል አገልግሎት መስጠት መጀመሩ ቀደም ሲል ናሙናዎች  ወደ አዲስ አበባ ተልከው ውጤቱ ለመጠበቅ ይወስድ የነበረውን ጊዜ እንደሚያስቀረው ተናግረዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም