ቀጥታ፡

የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ሰራተኛውና አሰሪው ወቅቱ የሚጠይቀውን ርብርብ በማድረግ መግታት እንደሚገባ ተገለጸ

አዲስ አበባ ሚያዚያ 20/2012(ኢዜአ) የዓለም የሙያ ደህነነትና ጤንነት ቀን በኢትዮጵያ ለ15ኛ በዓለም አቀፍ ደረጃ ደግሞ ለ16ኛ ጊዜ "ወረርሽኙን እንግታ፤ የስራ ቦታ ደህንነትና ጤንነት ህይወትን ይታደጋል'' በሚል መሪ ሃሳብ ተክብሯል።

የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትሯ ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬና ሌሎችም የስራ ሃላፊዎች ደም ለግሰዋል።

በአሁኑ ወቅት የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ መከሰቱን ተከትሎ አገራችንን ጨምሮ በርካታ የመንግስትና የግል መስሪያ ቤቶች ተዘግተዋል።

ሆኖም እንደ አስፈላጊነቱ አንዳንድ የመንግስትና የግል ተቋማት በስራ ላይ ይገኛሉ።

በኢትዮጵያ ለ15ተኛ ጊዜ ዛሬ የተከበረው የዓለም የሙያ ደህንነትና ጤንነት ቀን ትኩረቱን ያደረገው በዚሁ ወረርሽኝና በስራ ላይ ያሉ ሰራተኞች ላይ ትኩረት ባደረገ መልኩ ተስቦ ውሏል።

የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፣  በአሁኑ ወቅት ዓለምን እያስጨነቀ የሚገኘውን የኮቪድ 19 ወረርሽን ምላሽ ለመስጠትና የሰራተኞችን የስራ ቦታ ድህንነት ለማስጠበቅ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል።

''በአሁኑ ወቅት የስራው ዓለም የወረርሽኙ ስጋት የተደቀነበት መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሯ፣ ሰራተኛውና አገሪቱ ወቅቱ የሚጠይቀውን ርብርብ በማድረግ ወረርሽኙን መግታት ይገባል ብለዋል።

በሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል የወጣው ''የኮቪድ 19 የስራ ቦታ ምላሽ ፕሮቶኮል''   በየጊዜው ክትትል እየተደረገበት እንደሆነና እስካሁን ባለው ሁኔታም አመርቂ ውጤቶች እያታዩበት ነው ብለዋል።   

ይህም በአሰሪዎና ሰራተኞች በኩል መመሪያውን ተግባራዊ በማድረግ ለሙያ ደህነነትና ጤንነት እያሳዩ ያሉት መልካም ምላሽ ነው ብለዋል።  

የኢትዮጵያ ሰራተኛና ማህበራት ኮንፌደሬሽን ፕሬዝዳንት፣ አቶ ካሳሁን ፎሌ በበኩላቸው፣ ወረርሽኙ የሚተላለፈው በንክኪና በትንፋሽ በመሆኑ፣ የሰዎች መሰባሰብ የሚከለክል ወቅት ነው።

በመሆኑም በስራ ቦታ ወትሮ ከሚደረገው ጥንቃቄ በተለየ መልኩ ትኩረት ተሰጥቶት ሊሰራበት የሚገባው እንደሆነ አንስተዋል።

አብዛኛው አሰሪዎች የወረርሽኙን አስከፊነት በመገንዝብ፣ ለሰራተኞቻቸው አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ እያገዙ እንዳሉ ያነሱት አቶ ካሳሁን አንዳንድ አሰሪዎች ግን ምንም እንዳልተፈጠረ ጉዳዩን ቸል ያሉ እንዳሉም አንስተዋል።

በመሆኑም የወጣውን ፕሮቶኮልና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲተገበር የአዋጁ አስፈጻሚ አካላት ተገቢውን ቁጥጥር ሊያደርጉ እንደሚገባ አሳስበዋል።

እለቱም የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴርን፣  የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ አሰሪዎች ኮንፌዴሬሽን፣ የኢትዮጵያ ሰራተኛና ማህበራት ኮንፌዴሬሽንና የኢትዮጵያ አሰሪዎች ኮንፌዴሬሽን በተገኙበት ተከብሯል።

በመርሃ-ግብሩ ማጠቃለያ ላይ የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትሯ ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬን ጨምሮ ሌሎችም የስራ ሃላፊዎች ደም ለግሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም