ቀጥታ፡

በአፋር ክልል ህገወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመቆጣጠር የተጀመረው ጥረት ውጤት እያመጣ ነው

ሚያዚያ 20/2012 (ኢዜአ) አፋር ክልል ከጅቡቲ በሚያዋስኑት ወረዳዎች ህገወጥ የሰዎች ዝውውርን  ለመቆጣጠር የተጀመረው ጥረት አበረታች ውጤት እያመጣ መሆኑን የክልሉ የኮሮና መከላከል ግብረ ኃይል ገለጸ።

በጂቡቲ ካለው ሁኔታ ጋር በተያያዘም  የኢትዮ-ጂቡቲ ከባድ መኪና አሽከርካሪዎች የፊትና አፍንጫ  መሸፈኛ ጭምብል መጠቀምን መዘንጋት እንደሌለባቸው ግብረ ኃይሉ አሳስቧል።

የግብረ ኃይሉ አባልና የክልሉ ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ያሲን ሃቢብ እንደተናገሩት የኮሮና ቫይረስን በመስጋት ሰዎች በየቀኑ ከጅቡቲ ወደ ሀገር ውስጥ  ይገባሉ።

የሚገቡትን  በመቆጣጠር ከሰመራ ዩኒቨርሲቲው  በተጨማሪ ግብረ ኃይሉ በአፋምቦ ፣አይሳኢታ እና ኤሊደአር ወረዳዎች አራት የመግቢያ በሮች ጊዜያዊ ማቆያዎች አዘጋጅቶ ሰዎችን እየተቀበለ ነው ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት ከ450 በላይ ከጅቡቲ በህገወጥ መንገድ የገቡ ሰዎች በማቆያዎቹ መቀበላቸውን ያመለከቱት አቶ ያሲን  ከ14 ቀናት በላይ በማቆይትም ነጻ መሆናቸው ሲረጋገጥ ወደ ሚፈልጉት አካባቢ እንደሚሸኙ አስታውቀዋል።

ህገወጥ የሰዎች እንቅስቃሴ ሌላውን የህብረተሰብ ክፍል ለኮሮና ቫይረስ እንዳያጋልጠው የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎችን ፣የሀገር ሽማግሌዎችንና የኃይማኖት አባቶችን ባሳተፈ አግባብ የንቅናቄ ስራ እየተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም ህገወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመቆጣጠር  የተጀመረው ጥረት አበረታች ውጤት እያመጣ በመሆኑ ማጠናከር  እንደሚያስፈልግም አስታውቀዋል።

አቶ ያሲን እንዳሉት የሀገሪቱ ገቢና ወጪ ንግድ መስመር በሆነው ጋላፊ ኬላ ከሙቀት ልኬት ስራ በተጓዳኝ  ከባድ የጭነት ተሽከርካሪዎች ወደ ሀገር ሲገቡ የኬሚካል ርጭት እየተካሄደ ነው።

ርጭቱ ከተጀመረ አንድ ሳምንት እንደሆነው ጠቅሰው በቀን በአማካኝ ከ2ሺ በላይ ከበድ የጭነት ተሽከርካሪዎች የኬሚካል ርጭት እየተካሄደ  መሆኑን አስረድተዋል።

በተጨማሪም ለአሽከርካሪዎች ስለኮሮና ቫይረስ  ምንነት፣  መተላለፊያና መከላከያ መንገድ  ትምህርት እንደሚሰጥም  ገልጸዋል።

ከዚህም ሌላ አሽከርካሪዎቹ ከጅቡቲ አዲስ አበባ ሲመላለሱ ከተለያዩ  ሰዎች ጋር ንክኪና ግንኙነት ስለሚኖራቸው ለራሳቸውና ቤተሰቦቻቸው ብሎም ለሌላው ህብረተሰብ ጤንነት የፊትና አፍንጫ ጭምብል  መጠቀምን መዘንጋት እንደሌለባቸውም አሳስበዋል።

በተለይም ከጁቡቲ ወደ ኢትዮጵያ በሚገቡበት ወቅት በተለያዩ ከተሞች ለምሳና  ሻይ ቡና  በሚያርፉበት ወቅትም ጭምቡሉን በመጠቀም  ኃላፊነታቸውን እንዲወጡም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

"ባለሃብቶችም ለአሽከርካሪዎቻቸው ጭምብልና የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች ማሟላት ይጠበቅባቸዋል "ብለዋል

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም