ቱርክ ለኢትዮጵያ የንጽህና መጠበቂያ ቁሶች ድጋፍ አደረገች

70

አዲስ አበባ ሚያዚያ 20/2012 (አዜአ) ቱርክ ለኢትዮጵያ የኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19)ን ለመከላከል የሚያግዙ 1 ሺህ 700 ኪሎግራም የሚመዝኑ የተለያዩ ንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች ድጋፍ አደረገች።

ድጋፉን በኢትዮጵያ የቱርክ አምባሳደር ያፕራክ አልፕ ለሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ሚኒስቴር ዛሬ አስረክበዋል።

ድጋፉ የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል የሚያገለግሉ ጓንት፣ የእጅ ንጽህና መጠበቂያ ፣ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብሎችና ሌሎችን ያካተተ ነው።

በዚሁ ወቅት በኢትዮጵያ የቱርክ አምባሳደር ያፕራክ አልፕ የኢትዮጵያንና የቱርክን የቆየ ታሪካዊ ግንኙነት በማንሳት አገራቸው በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥም ከኢትዮጵያ ጎን እንደምትቆም ገልጸዋል።

ወደፊትም ድጋፋቸውን እንደሚቀጥሉ ነው አምባሳደሯ ያረጋገጡት።

የሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ሚኒስትር ወይዘሮ ፊልሰን አብዱላሂ ቱርክ ኢትዮጵያ የኮሮና አቫይረስን ለመከላከል እያደረገች ያለውን ጥረት ለማገዝ ላደረገችው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

በቀጣይም ኢትዮጵያ ለምትጠይቀው ድጋፍ ቱርክ አወንታዊ ምላሽ እንደምትሰጥ እምነታቸው መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም