በድሬዳዋ አስተዳደር ከ1 ሺህ ለሚበልጡ ወገኖች የምግብና የቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገ - ኢዜአ አማርኛ
በድሬዳዋ አስተዳደር ከ1 ሺህ ለሚበልጡ ወገኖች የምግብና የቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገ
ድሬዳዋ ፣ ነቀምቴ፣ ሰመራ ፣ ሚያዚያ 20/2012 (ኢዜአ) በድሬዳዋ አስተዳደር በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ለችግር ለተጋለጡ ከአንድ ሺህ በላይ ወገኖች የምግብና ንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስ ድጋፍ መደረጉ ተገለጸ።
በተመሳሳይ በአሮሚያ ቄለም ወለጋ የሚንቀሳቀሰው "ስታንድ ባይ ሚ’’ የተባለ ድርጅት እና የአፋር ህዝብ ፓርቲ ድጋፍ አድርገዋል።
የድሬዳዋ ቀበሌ ዜሮ አምስት ወጣቶች አስተባባሪ አቶ ቢንያም ታደሰ ከበጎ አድራጊዎች ገንዘብ አሰባስበው የገዙትን የምግብ ዘይት፣ ሩዝ፣ ማኮሮኒ የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስ ለ400 አቅመ ደካሞችና ችግረኞች ትናንት ማከፋፈላቸውን ተናግረዋል።
የቫይረሱን ጉዳት ለመቀነስ ከቀበሌው ጋር በመተባበር እንደሚሰሩም ገልፀዋል፡፡
ወጣቶቹ ድጋፍ ባደረጉበት ስነስርዓት ወቅት የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ ፈጡም ሙስጠፋና የአስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ አቶ አህመድ መሐመድና ሌሎችም የኮሮና መከላከል ግብረ ኃይል አካላት ተገኝተዋል።
የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አህመድ መሐመድ ወጣቶቹ ለሚያከናውኗቸው በጎ ተግባራት አስተዳደሩ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡
ድጋፍ ከተደረጋላቸው መካከል ወይዘሮ አሊያ ሀሰን የቤተሰባቸውን የወር የምግብ ቀለብ ማግኘታቸውን በመግለጽ ወጣቶቹን አመስግነዋል፡፡
እንዲሁም ብራ ኮፊ የተባለ የግል የንግድ ማህበር የረመዳንን ጾም ምክንያት በማድረግ በኮሮና ሳቢያ ለችግር ለተጋለጡ ለ700 ሰራተኞቹ አንድ ሚሊዮን 700ሺህ ግምት ያለው ሩዝ፣ የዳቦ ዱቄት፣ የምግብ ዘይትና ንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስ አከፋፍሏል፡፡
የድሬዳዋ አስተዳደር የኮሮና ቫይረስ መከላከል ግብረ ኃይል የድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ሱልጣን አልይ በአስተዳደሩ እስካሁን በጥሬ ገንዘብና በዓይነት 17 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ መገኘቱን ገልፀዋል፡፡
በተመሳሳይ በኦሮሚያ ቄለም ወለጋ ዞን ደምቢ ዶሎ ከተማ " ስታንድ ባይ ሚ’" የተባለ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ኮሮናን ለመከላከል እንቅስቃሴ በመገደቡ ምክንያት ለተቸገሩ 313 የቤተሰብ አባላት ድጋፍ ማድረጉን የከተማው አስተዳደር ገለጸ።
የአስተዳደሩ ሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ጽህፈት ቤት ኃላፊና የኮሮና መከላከል ግብረ ኃይል አባል ወይዘሮ ሙሉ እንዳሉት ድርጅቱ ለቤተሰብ አባላቱ ካደረገው ድጋፍ መካከል የጤፍ እህል፣ የዳቦ ዱቄት፣ ሩዝ፣ የምግብ ዘይትና ጥሬ ገንዘብ ይገኝበታል።
የድርጅቱ ማኔጀር ማነጀር አቶ ራጋ ታሲሳ ለ313 የቤተሰብ አባላት ያደረጉት ድጋፍ ከግማሽ ሚሊዮን በጥሬ ገንዘብና በዓይነት መሆኑን ተናግረዋል።
ድጋፍ ከተደረገላቸው መካከል የከተማው ቀበሌ አምስት ነዋሪ ወይዘሮ ጎዴ ዳባ በሰጡት አስተያየት የተሰጣቸው ድጋፍ እንደ ቤተሰባቸው ብዛት እንደሆነ ገልጸው 800 ብር ጥሬ ገንዘብ እንዳገኙ በመጥቀስ ድርጅቱን አመስግነዋል።
ሌላው ነዋሪ አቶ ደስታ ገመዳ በበኩላቸው ከምግብና ቁሳቁስ ድጋፍ ሌላ 400 ብር በጥሬ ገንዘብ እንደተሰጣቸው ተናግረዋል።
በሌላ በኩል የአፋር ህዝብ ፓርቲ (አህፓ) ከ200ሺ በላይ ብር የሚገመት የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስ ድጋፍ ለክልሉ ጤና ቢሮ አስረከበ።
የፓርቲው ስራ አስፈጻሚ አባል አቶ ሁሴን ደቶና እንደገለጹት ፓርቲው ሊኖር የሚችለው መጀመሪያ እወክለዋለሁ የሚለውን የህብረተሰብ ክፍል ሀገር ደህንነትና ህልውናው ሲጠበቅ ብቻ ነው።
ለዚህም ፓርቲው 200ሺህ ብር የሚገመት ሳኒታይዘርና ፈሳሽ ሳሙና ድጋፍ ማድረጉን ገልጸው በቀጣይም አባላቱንና ደጋፊዎችን በማስተባበር ተጨማሪ እገዛ ለማድረግ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ተናግረዋል።
የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊና የኮሮና መከላከል ግብረ-ኃይል ጸሐፊ ዶክተር ፈረጅ ረቢሳ የአፋር ህዝብ ፓርቲ በሽታውን ለመከላከል እንዲያግዝ ያደረገው ድጋፍ ሌሎችንም የሚያነሳሳ መሆኑን ገልጸዋል።
ድጋፉንም በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች እንዲደርስ ቢሮው ኃላፊነቱን እንደሚወጣ አስታውቀዋል።