የተበላሹ 24 የመተንፈሻ መርጃ መሳሪያዎች ተጠግነው ለአገልግሎት ብቁ ሆኑ - ኢዜአ አማርኛ
የተበላሹ 24 የመተንፈሻ መርጃ መሳሪያዎች ተጠግነው ለአገልግሎት ብቁ ሆኑ
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 19/2012( ኢዜአ) በጤና ሚኒስቴር እና በኢትዮጵያ አየር መንገድ ትብብር በብልሽት ከአገልግሎት ውጭ የነበሩ 24 የመተንፈሻ መርጃ መሳሪያዎች (ቬንትሌተሮች) ተጠግነው ለአገልግሎት ብቁ ሆኑ።
በአሁኑ ወቅት የተከሰተውን የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ተከትሎ ኢትዮጵያ ያጋጠማትን የመተንፈሻ መርጃ መሳሪያዎች እጥረት ለመፍታት አንዱ አማራጭ የተበላሹትን ጠግኖ ለአገልግሎት ማብቃት በመሆኑ በተለያዩ ድርጅቶች የጥገና ሥራዎች በመከናወን ላይ ናቸው።
በኢትዮጵያ 197 የፅኑ ሕሙማን የመተንፈሻ መርጃ መሳሪያዎች ወይም ቬንትሌተሮች በብልሽት ምክንያት መቆማቸውን የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ ተናግረዋል።
ከእነዚህ መካከል ከተለያዩ ሥፍራዎች የተሰበሰቡና ከ40 በላይ የሚሆኑ መሳሪያዎችን ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ሜዲካል ኢንጂነሮች ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጥገና ባለሙያዎች ጋር በመተባበር በአየር መንገዱ የጥገና አገልግሎት ክፍል እየጠገኑ ይገኛሉ።
በዚህም አስካሁን ድረስ 24 መሳሪያዎች ተጠግነው ለአገልግሎት ብቁ መሆናቸውን ዛሬ ሚኒስትሯ የጥገና ማዕከሉን በጎበኙበት ወቅት ተናግረዋል።
እንደ ዶክተር ሊያ ገለጻ ከተለያዩ ሆስፒታሎች የተሰበሰቡ 24 የመተንፈሻ መርጃ መሳሪያዎች በኢትዮጵያ አየር መንገድ ቴክኒሺያኖች በኩል ጥገና ተደርጎላቸው ለአገልግሎት ብቁ ሆነዋል።
ይህም ለሕሙማን የሕክምና ድጋፍ ለማድረግ የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝ፣ ወጪ ቆጣቢና ትልቅ አቅም የሚፈጠር መሆኑን ነው የገለጹት።
ኢትዮጵያ ያለባትን የመሳሪያዎች እጥረት በእርዳታና በግዥ ለማቃለል ከምታደርገው ጥረት በተጨማሪ በአየር መንገዱና በጤና ሚኒስቴር ትብብር የተጀመረውን ሥራ በማጠናከር ቀሪ መሳሪያዎችንም ጠግኖ ሥራ ላይ ለማዋል ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።።
አየር መንገዱ በክልሎች በሚገኙ ሆስፒታሎች በብልሽት የቆሙ መሳሪያዎችን በነጻ በማጓጓዝም ላደረገው ጥረት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ከኢትዮጵያ አየር መንገድ በተጨማሪ ሌሎች መንግስታዊ ተቋማትና ሆስፒታሎችም የተበላሹ መሳሪያዎችን በመጠገን ወደሥራ እያስገቡ መሆኑን ዶክተር ሊያ ጠቁመዋል።
በአየር መንገድ ግሩፕ የኤርፖርቶች ድርጅት ሥራ አስኪያጅ አቶ እስክንድር ዓለሙ በበኩላችው አየር መንገዱ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት የሚደርሰውን ጉዳት ለመቀነሰ የበኩሉን ሚና እየተወጣ መሆኑን ገልጸዋል።
ከኢትዮጵያ አልፎም በመላው ዓለም መድኃኒቶችንና የሕክምና መሳሪያዎችን የማጓጓዝ ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን ግልጸው፣ "የመተንፈሻ መርጃ መሳሪያዎችን ጥገና አገልግሎትም ሰው የማትፈር ጉዳይ በመሆኑ እየሰራ ነው" ብለዋል።
ወደፊትም ድርጅቱ ጥረቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።