ቀጥታ፡

ማህበሩ ኮቪድ 19 ን ለመከላከል ከ7 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው የቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ

ሚያዝያ 19/2012 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ኮቪድ 19ን ለመከላከል ከ7 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ፡፡ 

ድጋፉ ከዓለም አቀፍ ቀይ መስቀል ኮሚቴ ባደረገው ትብብር መገኘቱን አስታውቋል፡፡

የማህበሩ ዋና ጸሐፊ ዶክተር መሸሻ ሸዋረጋ ማህበሩ ዛሬ ለብሔራዊ ድጋፍ አሰባሳቢ ግብረ-ኃይል ሲያስረክቡ እንደተናገሩት ድጋፉም በፌደራል ደረጃና በክልል ደረጃ ወረርሽኙን ለመከላከል ይረዳል፡፡

በድጋፉ 2ሺ500 ፍራሽ፣ 2ሺ500 የብርድ ልብስና አንሶላ፣ የመተኛ ከረጢት ተካተዋል።

እንዲሁም ሳሙናና ሳኒታይዘርን ጨምሮ የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስ እንደሚገኙበት ዶክተር መሸሻ ጠቁመዋል፡፡

ማህበሩ የበሽታውን መስፋፋት ለመግታትና ለኅብረተሰቡ ግንዛቤ  ለማስጨበጥ  ከ12ሺህ  በላይ በጎ ፈቃደኞችን ማሰማራቱን ገልጸዋል።

በጎ ፈቃደኞቹ  ኅብረተሰቡ የእጅ  መታጠብ ባህልን እንዲያዳብር መርዳታቸውን  ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም ከ32ሺህ በላይ ለሚሆኑ ወገኖች የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስና የምግብ  ድጋፍ ማድረጉንም አስታውሰዋል፡፡

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ  ሚኒስትርና የብሔራዊ ድጋፍ አሰባሳቢ ግብረ-ኃይል አባል  ዶክተር  አብርሃም ማህበሩ ላደረገው ድጋፍ አመስግነዋል።

ማህበሩ ለሌሎች  ተቋማት  ባሳየው አርዓያነትም አድናቆታቸውን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም