ቀጥታ፡

በብልሽት ከአገልግሎት ውጭ የነበሩ 24 የመተንፈሻ መርጃ መሳሪያዎች ተጠገኑ

አዲስ አበባ ፤ሚያዚያ 19/2012 (ኢዜአ)በብልሽት ምክንያት ከአገልግሎት ውጭ የነበሩ 24 የመተንፈሻ መርጃ መሳሪያዎች (ቬንትሌተርስ) በኢትዮጵያ አየር መንገድና ጤና ሚኒስቴር ትብብር ተጠግነው ለአገልግሎት ዝግጁ ሆኑ።

የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ የአየር መንገዱን የመሳሪያ ጥገና ክፍል ዛሬ ጎብኝተዋል። 

መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት 190 የሚደርሱ የመተንፈሻ መርጃ መሳሪያዎች በብልሽት ምክንያት ያለ አገልግሎት ተቀምጠዋል።

ከእነዚህ ውስጥ ከተለያዩ ሆሰፒታሎች የተሰበሰቡትን 24 የመተንፈሻ መርጃ መሳሪያዎች በኢትዮጵያ አየር መንገድ ቴክኒሺያኖች ጥገና ተደርጎላቸው ለአገልግሎት በቅተዋል።

በአየር መንገዱና በጤና ሚኒስቴር ትብብር በተጀመረው ስራ ቀሪዎችንም ጠግኖ ስራ ላይ ለማዋል ጥረት እየተደረገ ይገኛል።

በኢትዮጵያ አየር መንገድ ይህ ጥገና የሚከናወንበትን የጥገና ክፍል በዛሬው እለት የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ጎብኝተዋል።

የአየር መንገዱ የጥገና ክፍል ከመደበኛ ስራው ባሻገር በየሆስፒታሉ ተበላሽተው የቆዩ 30 የመተንፈሻ መርጃ መሳሪያዎችን እየጠገነ መሆኑን ከዚህ ቀደም መግለጹ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም