በ15 ከተሞች አጋጥሞ የነበረው የመብራት መቋረጥ ጊዜያዊ መፍትሔ አገኘ - ኢዜአ አማርኛ
በ15 ከተሞች አጋጥሞ የነበረው የመብራት መቋረጥ ጊዜያዊ መፍትሔ አገኘ
ማይጨው ሚያዚያ 19 ቀን 2012 /ኢዜአ/ በትግራይ ደቡባዊ ዞን እና በአማራ ክልል ላሊበላና ስቆጣ ከተሞች ለአምስት ቀናት ተቋርጦ የነበረው የኤሌክትሪክ አገልግሎት ችግር ጊዜያዊ መፍትሔ ማግኘቱን በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የሰሜን ሪጅን ድስትሪክት ገለጸ።
የዲስትሪክቱ ዳይሬክተር አቶ ሮቤል ገብረ እግዚአብሔር ለኢዜአ እንደገለጹት በአላማጣ የሚገኘው የሃይል ማከፋፋያ ትራንስፎርመር ተቃጥሎ በትግራይ ደቡባዊ ዞንና በአማራ ክልል የሚገኙ ከተሞች ለአምስት ቀናት የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተቋርጦባቸው ቆይቷል።
በትግራይ አላማጣና ማይጨው በአማራ ክልል ደግሞ ላሊበላና ሰቆጣ ከተሞችን ጨምሮ የኤሌክትሪክ አገልግሎቱ በ15 ከተሞች ተቋርጦ ነበር ።
አገልግሎቱ የተቋረጠው በአላማጣ ከተማ የሚገኝ ባለ 21 ጌጋ ዋት ሀይል ተሸካሚ ትራንስፎርመር በመቃጠሉ ሲሆን በአሁን ጊዜ በ12 ጌጋ ዋት ሀይል ተሸካሚ ትራንስፎርመር ተተክቶ የችግሩን ሀኔታ 80 በመቶ ማቃለል እንደተቻለ ዳይሬክተሩ ተናግረዋል ።
የተተካውን ትራንስፎርመር የሀይል ጫና በሚበዛበት ወቅት ሁሉንም በአንድ ጊዜ ማስተናገድ ስለማይችል ከተሞቹ በፈረቃ እንዲጠቀሙ መደረጉን ነው ያስረዱት ።
የተከሰተውን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት የሚችል ባለ 21 ጌጋ ዋት ትራንስፎርመር በመገኘቱ ችግሩን በሁለት ሳምንታት ውስጥ ሙሉ ለሙሉ ለመፍታት እየተሰራ ነው ብለዋል።
የማይጨው ከተማ 04 ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ ሮማን ሕሉፍ በሰጡት አስተያየት ለአምስት ቀናት ያህል የነበረውን ችግር መቃለሉን ገልፀዋል።
አሁን የተለቀቀው የኤሌክትሪክ አገልግሎት የመጠጥ ውሀ የሚመረትባቸው ጉድጓዶች በሀይል እጥረት ምክንያት ማንቀሰቀስ አለመቻሉን የተናገሩት ደግሞ የማይጨው ከተማ ውሀ አቅርቦት ጽህፈት ቤት ስራ አስኪያጅ አቶ ሀይለ ተሰማ ናቸው።
የመብራት አገልግሎት ቢለቀቅም ኃይል ስለሌለው የንጹህ መጠጥ ውሀ አቅርቦቱ ለሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ለማዳረስ እንቅፋት እንደሆነባቸው ተናግረዋል ።
የኮሮና ቫይረስ ለመከላከል የእጅ ንፅህና መጠበቅ አስፈላጊ ነው እየተባለ ውሃ መጥፋቱ ተገቢ ባለመሆኑ ችግሩን በዘላቂነት እንዲፈታላቸው ጠይቀዋል።
በጄኔሬተር በመታገዝ ቀን ላይ ውሃው በጋኖች እንዲጠራቀም በማድረግ ማታ ላይ ለሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የማዳረስ ስራ እየተከናወነ መሆኑንም አቶ ሀይለ ተናግረዋል።
በሆስፒታልና በማረሚያ ቤት ደግሞ በጄኔሬተር አማካኝነት ያለማቋረጥ ንጹህ የመጠጥ ውሃ እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል።