የጃክ ማ የአፍሪካ ሶስተኛ ዙር የኮቪድ 19 መከላከያ የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ አዲስ አበባ መግባት ጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
የጃክ ማ የአፍሪካ ሶስተኛ ዙር የኮቪድ 19 መከላከያ የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ አዲስ አበባ መግባት ጀመረ
አዲስ አበባ ፤ሚያዚያ 19/2012 (ኢዜአ) ቻይናዊው ባለፀጋ የአሊባባ ፋውንዴሽን መስራችና ስራ አስፈጻሚ ጃክ ማ ለአፍሪካ አገራት ሶስተኛውን ዙር የኮቪድ 19 መከላከያ የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ አዲስ አበባ መግባት ጀመረ።
በዛሬው እለት 61 ሺህ ኪሎ ግራም ቁሳቁስ አዲስ አበባ የደረሰ ሲሆን ቀሪውም በቀጣዮቹ ቀናት ይገባል ተብሎ ይጠበቃል።
ከከአሁን በፊትም ለአፍሪካ አገራት የተለያዩ ቁሳቁሶች ድጋፍ ያደረጉት ጃክ ማ በሶስተኛው ዙር ዕርዳታቸው አይነተ ብዙ የህክምና ግብዓቶችን ልከዋል።
በዛሬው እለትም ለ54ቱ የአፍሪካ አገራት የሚዳረስ 61 ሺህ ኪሎ ግራም የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ አዲስ አበባ ገብቷል።
በቀጣዮቹ ቀናት ቁሳቁሱን እንደተለመደው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለሁሉም የአፍሪካ አገራት የሚያዳርስ ይሆናል።
ጃክ ማ የለገሱት የሶስተኛው ዙር ቀሪ ቁሳቁሶችም በቀጣዮቹ ጥቂት ቀናት ተጠቃለው አዲስ አበባ የሚገቡ መሆኑ ታውቋል።
የአሁኑ ድጋፍ 4 ነጥብ 6 ሚሊየን የአፍና አፍንጫ መሸፈኛዎች፣ 500 ሺህ መመርመሪያዎች፣ 300 የመተንፈሻ መሳሪያዎች፣ 2 ሺህ የሙቀት መለኪያዎች፣ 400 ሺህ የህክምና አልባሳትና የፊት መሸፈኛዎች፣ 100 የሙቀት መለኪያዎችና 500 ሺህ ጥንድ የእጅ ጓንቶችን ያካተተ ነው።
በመጀመሪያው ዙር ጃክ ማ 20 ሺህ መመርመሪያዎች፣ 100 ሺህ የአፍና ፊት ጭምብሎች፣ 1 ሺህ የህክምና ባለሙያ አልባሳት ለግሰዋል።
በሁለተኛው ዙር ደግሞ 500 የመተንፈሻ መሳሪያዎች፣ 200 ሺህ የፊት መሸፈኛዎችና አልባሳት፣ 1 ሚሊየን ናሙና መውሰጃ፣ 2 ሺህ የሙቀት መለኪያና 500 ሺህ ጓንቶችን መለገሳቸው ይታወሳል።