ድርጅቶቹ በአማራ ክልል ለኮሮና ቫይረስ ለመከላከል 22 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረጉ - ኢዜአ አማርኛ
ድርጅቶቹ በአማራ ክልል ለኮሮና ቫይረስ ለመከላከል 22 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረጉ
ባህርዳር ሚያዚያ 19/2012 የአማራ ብድርና ቁጠባ ተቋምና የአማራ የልማት ድርጅቶች ኮሮናን ለመከላከል የሚያግዝ 22 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር በጥሬ ገንዘብና በአይነት ድጋፍ ማድረጋቸውን አስታወቁ።
የአማራ ብድርና ቁጠባ ተቋም ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ መኮንን የለውምወሰን ዛሬ ድጋፉን ባስረከበቡበት ወቅተ እንዳሉት የኮሮና ወረርሽኝ የፋይናንስ ሴክተሩን እየጎዳው ይገኛል።
የበሽታውን ስርጭት ለመግታት በተለየ መንገድ መደጋገፍ እንደሚያስፈልግ ጠቅሰው ተቋሙ ለክልሉ የኮሮና መከላከል ኮማንድ ፖስት የ15 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አድርጓል።
በተጨማሪም ሞጣ፣ ቻግኒ፣ አዴት፣ አይከልና ገረገራ የሚገኙ ባለሁለትና ባለአራት ወለል አምስት የተቋሙ ህንፃዎች ለለይቶ ማቆያና ለህክምና አገልግሎት እንዲውሉ በጊዜያዊነት እንደተሰጠ ገልፀዋል።
ባለፉት ጊዜያትም የዕለት ጉርስ ለሌላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች 152 ሺህ ብር ግምት ያላቸው ዱቄት፣ የምግብ ዘይትና የንፅህ መጠበቂያ ሳሙና መለገሱን አስታውሰዋል።
በሽታው በቁጥጥር ስር እስኪውል ድረስ ተቋሙ የጀመረውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አቶ መኮንን አስረድተዋል።
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የኮሮና መከላከል ግብረ ኃይል ሰብሳቢ ዶክተር ፋንታ ማንደፍሮ በበኩላቸው ህዝባዊ ተቋማትን መገንባት በችግር ጊዜ ፈጥነው እንዲደርሱ ያግዛል ።
በክልሉ የሚገኙ የህዝብ ተቋማት ፣ ድርጅቶችና ባለሃብቶች ኮሮናን በመከላከል አጋርነታቸውን በማሳየት ላይ እንደሚገኙ ገልፀዋል ።
የአማራ ብድርና ቁጠባ ተቋም አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ በማድረግ ከክልሉ ህዝብ ጎን ይገኛል ያሉት ደግሞ የክልሉ ገንዘብና ኢኮኖሚ ቢሮ ኃላፊና የኮሮና ቫይረስ ሃብት አሰባሳቢ ዘርፍ ኃላፊ ዶክተር ጥላሁን መሀሪ ናቸው
የኮሮና ቫይረስ ሙሉ በሙሉ መከላከልእስኪቻል ድረስ ባለሃብቶችና ድርጅቶች ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርዋል።
በተመሳሳይ የአማራ ክልል የመንግስት የልማት ድርጅቶች ለኮረና ቫይረስ መከላከል 7 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር ወጪ የተደረገበት የምግብ እህል ድጋፍ አድርጓል።
የደርጅቶች ድጋፍና ክትትል ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መጋቢያው ጣሰው ድጋፉን ዛሬ ለክልሉ አደጋ መከላከል፣ ምግብ ዋስትና ልዩ ድጋፍ ለሚሹ የህብረተሰብ ክፍል ኮሚሽን አስረክበዋል።
ድጋፉ የክልሉ የልማት ድርጅቶች ቫይረሱ ሊያደርስ የሚችለውን ሰብአዊ ችግር ለመከለካል ያለመ ነው።
4 ሺህ 600 ኩንታል በቆሎ ድጋፍ መደረጉን የገለጹት አቶ መጋቢያው የልማት ድርጅቶቹ ህብረተሰቡን ሊደርስበት ከሚችል አደጋ ለመከላከል ከመንግስት ጋር በመሆን በትኩረት እየሰሩ ነው።
የመንግስት የልማት ድርጅቶች ያደረጉት ድጋፍ የሚያስመሰግንና አርአያ ሊሆን የሚገባ ተግባር ነው ያሉት ደግሞ የአማራ ክልል አደጋ መከላከል፣ምግብ ዋስትናና ልዩ ድጋፍ የሚሹ የህብረተሰብ ክፍሎች ማስተባበሪያ ኮሚሽን ኮሚሽነር ዘላለም ልጅአለም ናቸው።
የኮሮና ቫይረስ ለመከላከል በተከናወነ የገቢ ማሰባሰብ ስራ በክልሉ ከ150 ሚሊዮን ብር በላይ በአይነትና በጥሬ ገንዘብ መሰብሰብ እንደተቻለ ተገልጿል ።