በቅርቡ ተከስቶ የነበረው የቢጫ ወባ ወረርሽኝ በቁጥጥር ስር ዋለ - ኢዜአ አማርኛ
በቅርቡ ተከስቶ የነበረው የቢጫ ወባ ወረርሽኝ በቁጥጥር ስር ዋለ
አዲስ አበባ ፤ሚያዚያ 19/2012 (ኢዜአ) በደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰብና ህዝቦች ክልል ጉራጌ ዞን ውስጥ ተከስቶ የነበረው የቢጫ ወባ ወረርሽን በቁጥጥር ስር መዋሉን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።
ወረርሽኙ በተከሰተበት አካበቢ ለሚኖሩ ከ27 ሺህ በላይ ሰዎች ክትባት መሰጠቱም ተገልጿል።
የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደተናገሩት፤ በደቡብ ክልል በጉራጌ ዞን በእኖር ኤነር እና እነሞርና ኤነር ወረዳዎች የቢጫ ወባ ወረርሽኝ መከሰቱን የሚገልጽ ሪፖርት የካቲት 24 ቀን 2012 ዓ.ም ሪፖርት ተደርጓል።
ሪፖርት መቅረቡን ተከትሎ የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከክልሉ ጤና ቢሮ እና ከዞኑ ጤና መምሪያ ጋር በመሆን ለወረርሽኙ ምላሽ ሲሰጥ መቆየቱን ገልጸው፤ የበሽታው የመጨረሻ ምልክት መጋቢት 20 ቀን 2012 ዓ.ም እንደታየ ተናግረዋል።
''በአጠቃላይ 86 ሰዎች በበሽታው እንደተያዙ ተረጋግጧል'' በማለት፤ ከእነዚህ ውስጥ የአራት ሰዎች ህይወት ማለፉን ነው የተናገሩት።
ወረርሽኙ በስፋት በተከሰተባቸው ቀበሌዎች የቤት ለቤት ቅኝት በማድረግ ለ27 ሺህ 177 ግለሰቦች የቢጫ ወባ መከላከያ ክትባት መሰጠቱንም ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት ወረርሽኙን መቆጣጠር መቻሉን ገልጸው፤ ''ከመጋቢት 20 ጀምሮ በበሽታው እንደተያዘ ሪፖርት የተደረገ አዲስ ታማሚ የለም'' ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን በመከላከል ስራ ላይ በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሯ፤ ከዚህ በተጓዳኝ መደበኛ የህክምና አገልግሎቶች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ አሳስበዋል።
''እናቶች በህክምና ተቋማት መውለዳቸውንና ህጻናት ተገቢውን ክትባት መውሰዳቸውን በየጊዜው ማረጋገጥ ይገባል'' ሲሉም ተናግረዋል።
''ለዚህ ደግሞ የህክምና ባለሙያዎች ድርብ ሃላፊነት አለባቸው'' ብለዋል።