አሚሶም በሶማሊያ ተልእኮ ቆይታው ዙሪያ ምክክር አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
አሚሶም በሶማሊያ ተልእኮ ቆይታው ዙሪያ ምክክር አደረገ
አዲስ አበባ ፤ሚያዚያ 19/2012 (ኢዜአ) በአፍሪካ ህብረት የሶማልያ ሰላም አስከባሪ ሃይል (አሚሶም) በሶማሊያ ያለውን ቆይታ አስመለክቶ የቪዲዮ ውይይት ማድረጉ ተገለጸ።
በአፍሪካ ህብረት የሶማልያ ሰላም አስከባሪ ሃይል (አሚሶም) በሶማሊያ ያለውን ቆይታ አስመልክቶ የቪዲዮ ውይይት አድርጓል።
የተልዕኮው አስተባባሪ ኮሚቴና የሰላም አስከባሪ ሰራዊት ያዋጡ አገራት ከሶማሊያ ፌደራላዊ መንግስት ጋር በተልዕኮው ዙሪያ 30ኛ መደበኛ ምክክር አድርገዋል።
ውይይቱ የአፍሪካ ህብረት ለሶማሊያ የሚያደርገውን ቀጣይ ድጋፍ በተመለከተ ይሁንታውን በሚቸርበትና በአሚሶም ስልጣን ዙሪያ ያተኮረ ነበር።
በተለይ በሶማሊያ ያለው ደህንነትና ጸጥታ ካለንበት ጊዜ አንስቶ እኤአ በ2021 ምን ሊመስል እንደሚችል፣ የአሚሶም ትኩረት እስከ ታህሳስ 2013 ምን ላይ ማረፍ እንዳለበት ያተኮረ ምክክር መደረጉ ተገልጿል።
ሶማሊያ እኤአ ከ2021 በኋላ ምን አይነት የደህንነት ስጋት ሊያጋጥማት ይችላል በሚለው ላይም ውይይት ተደርጓል።
እስካሁን አሚሶም ያገኛቸው ስኬቶች እንዳይቀለበሱ በሚረዱ ጉዳዮች ዙሪያም አመርቂ ምክክር አድርገዋል።
ለዚህም ጎረቤት አገራት ሊያደርጉት በሚችለው አስተዋጽኦ ዙሪያና ትብብር፣ ለአሚሶም የሚያስፈልገውን ሐብትን ውጤታማ በሆነ መንገድ ማንቀሳቀስና መጠቀምን እንዲሁም የፋይናንስ እገዛ እጥረትን አስመልክቶ መክረዋል።
ከዚህ በተጨማሪ አሚሶም ያከናወነውን የተሳካ ዘመቻ በማስመልከት የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት የተላለፈ ሲሆን ሰራዊቱ ስትራቴጂካዊ መንደር የሆነችውን ገናሌን መቆጣጠር መቻሉ ተወድሷል።
ለዚህ ስኬት መስዋዕትነት የከፈሉ የአሚሶም ሰራዊት አባላትም ዘላለማዊ ክብር እንደሚገባቸው ተወስቷል።
የሶማሊያን ሰላም ዘላቂ ለማድረግ ያለውን የሰራዊት ቁጥር መቀነስ ተገቢ አለመሆኑም በጉባኤው ስምምነት እንደተደረሰበት ተወስቷል።
የአፍሪካ ህብረት አሚሶምን በስፋት ለመደገፍ የያዘውን አቅጣጫና ሶማሊያን ለመደገፍ የሚያከናውነውን ዘርፈ ብዙ እገዛም አድንቀዋል።
ህብረቱ ወታደራዊ ሰልጠና በመስጠት፣ በማማከርና የጋራ ዘመቻ በማከናወን እንዲሁም የአሚሶምን ስልጣን መሰረት በማድረግ ወታደራዊና ፖሊሳዊ እገዛ እንዲያደርግ ተጠይቋል።
በውይይቱ አሚሶም በተለየ መልኩ በመከላከያ እዝ አሰጣጥና ቁጥጥር ላይ አበክሮ መስራትና ማጠናከር እንደሚገባው ተገልጿል።
ተልዕኮው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ አሉታዊ ጉዳት እንዳደረሰበት፣ በተለይ የመዘዋወር መብት መገደቡ፤ የወታደራዊ ኃይል እገዛ (በቱርክ፣ እንግሊዝ፣ አውሮፓ ህብረት እና አሜሪካ) ሊሰጥ የነበረ ሰልጠና መስተጓጎሉ ተግዳሮት መሆኑ ተነስቷል።
ቻይና እና ኮሪያ ኮቪድ 19 ወረርሽኘን ለመከላከል ለአሚሶም ያደረጉትን አስተዋጽኦ ጉባኤው አወድሶታል።
የአፍሪካ ህብረት ከፍተኛ ልዑክ ለአሚሶም የሚያስፈልገውን ስንቅና ትጥቅ በተለይ እስከ ታህሳስ 2013 እና በቀጣይ ወራት በተሟላ መልኩ በሚቀርብበት ሁኔታ ዙሪያ ከተቻለ ጉባኤ በመጥራት እንደሚመክር ጉባኤው አሳስቧል።
.