ሶማሌ ክልል ከተፈጥሮ ጋዝ ልማት ጋር በተያያዘ 'በሰው ላይ ጉዳት ደርሷል' በሚል የቀረበው ዘገባ መሰረተ ቢስ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ሶማሌ ክልል ከተፈጥሮ ጋዝ ልማት ጋር በተያያዘ 'በሰው ላይ ጉዳት ደርሷል' በሚል የቀረበው ዘገባ መሰረተ ቢስ ነው
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 19/2012( ኢዜአ) በሶማሌ ክልል ከተፈጥሮ ጋዝ ልማት ጋር በተያያዘ 'በሰው ላይ ጉዳት ደርሷል' በሚል በውጭ መገናኛ ብዙሃን የቀረበው ዘገባ መሰረተ ቢስ ነው ሲል የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር ገለጸ።
ተቋሙ ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳስታወሰው፤ የእንግሊዝ የዜና ምንጭ ዘጋርዲያን እ.ኤ.አ የካቲት 20 ቀን 2020 እትሙ 'በኦጋዴን ካሉብና ሂላላ በተባሉ አካባቢዎች እየተካሄደ ባለው የተፈጥሮ ጋዝ ልማት ምክንያት በተከሰተ የውሃ መበከል በአካባቢው ህዝብ ላይ በሽታ በማስከተል እስካሁን ከ2 ሺህ በላይ ሰዎች ህይወታቸው አልፏል' የሚል ዘገባ አውጥቷል።
ይህንኑ ዘገባ ቢቢሲ እንደ ጎርጎሮሳውያን አቆጣጠር መጋቢት 2 ቀን 2020 እትማቸው ማስተጋባቱን እንዲሁ።
የተፈጥሮ ጋዙን የሚያለማው ፖሊ ጂሲል ኩባንያ ለተፈጥሮ ጋዝ ልማት ወደ አገር በሚያስገባቸው ኬሚካሎች ምክንያት ደርሷል የተባለው የውሃና አካባቢ መበከል ያስከተለው ጉዳት በጋዜጦች ተዘርዝሯል።
በዚህም በሰዎች ላይ ያስከተለው በሽታ፣ ድንገተኛ ትኩሳት፣ ራስ ምታት፣ አይን ቢጫ በማድረግና በሌሎች ምልክቶች ለሞት እንደሚዳርግ መሆኑን በመግለጽ በዘገባቸው አስፍረውታል።
የቀረበውን ዘገባ ለማጣራት ከአካባቢ፣ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን እንዲሁም ከሌሎች አካላት የተውጣጣ የጥናት ቡድን የተፈጥሮ ጋዝ በሚለማበት አካባቢ ማጣራት ማድረጉን ሚኒስቴሩ አስታውቋል።
ኩባንያው ወደ አካባቢው ከገባ በኋላ ሙቀት መጨመር፣ ዝናብ መጥፋትና የተለያዩ የአየር ንብረት ለውጦች መታየታቸውንና አዳዲስ በሽታዎች መከሰታቸውን የአካባቢው ማህበረሰብ ተወካዮች ገልጸዋል።
በውሃና በአካባቢ ብክለት ታመዋል የተባሉ አምስት ሰዎች ሁሉም በተለያየ በሽታ የታመሙ መሆናቸው የተጠቀሰ ሲሆን፤ የክልሉ ጤና ቢሮም በአካባቢው ከተለመዱ በሽታዎች ውጪ አዲስ የተከሰተ በሽታ አለመኖሩን አረጋግጧል።
ቡድኑ በአካባቢው ፖሊ ጂሲል ኩባንያ ያስቆፈራቸው ሁለት የውሃ ጉድጓዶች ችግር እንዳሌላባቸውና አገልግሎት እየሰጡ መሆኑንም ተጠቅሷል።
የተፈጥሮ ጋዝ ጉድጓዶች አያያዝ፣ የተረፉ ግብዓቶችና ከጉድጓድ የሚወጡ ዝቃጮች አወጋገድ ዓለም ዓቀፍ ደረጃውን የጠበቀ መሆኑን የጥናት ቡድኑ ባደረገው ምልከታ መታዘቡን ሚኒስቴሩ ገልጿል።
በመሆኑም ዘጋርዲያን በየካቲት 20 ቀን 2020 እትሙ ያቀረበውንና ቢቢሲ ያስተጋባው ስሞታ ከእውነት የራቀና መሰረተ ቢስ በመሆኑ የማስተካከያ እርምት እንዲያደርጉ ሚኒስቴሩ ጠይቋል።