ቀጥታ፡

በአፋር ክልል ኮሮናን ለመከላከል ከ40ሚሊዮን ብር በላይ በጥሬ ገንዘብና በዓይነት ድጋፍ ተገኘ

አፋር፤ ሚያዚያ 19/2010 (ኢዜአ) በአፋር ክልል የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የሚያግዝ ከ40ሚሊዮን ብር በላይ በጥሬ ገንዘብና በዓይነት ከባለሃብቶችና ተቋማት በድጋፍ መገኘቱን የክልሉ የኮሮና ቫይረስ መከላከል ግብር-ኃይል አስታወቀ።

የግብረ ኃይሉ አባልና የክልሉ ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ መሃመድ ሀሰን እንደገለጹት የክልሉ መንግስት በሽታውን ለመከላከል የተለያዩ ባለድርሻ አካላት፣ ባለሃብቶችና ተቋማትን ያሳተፈ የሃብት ማፈላለግ ስራ ሲያከናውን ቆይቷል።

እስካሁን በተደረገው ጥረት 14 ሚሊዮን 200ሺህ ብር በጥሬ ገንዘብ እና ከ26 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት በዓይነት ድጋፍ መገኘቱን አስታውቀዋል።

በዓይነት ከተገኘው ውስጥ ሩዝ፣ የምግብ ዘይት ፣ ፓስታ፣ ማካሮኒ እና የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች ይገኙበታል።

ድጋፉን ያደረጉት ባለሃብቶች ፣መንግስታዊና መንግሰታዊ ያልሆኑ ተቋማት መሆናቸውን አቶ መሃመድ ተናግረዋል።

በዓይነት የተገኘው ድጋፍ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙና አቅመ ደካሞችን በመለየት ወደ ማስራጨት ስራ መገባቱንም ገልጸዋል።

ከበሽታው ጋር ተያይዞ የህብረተሰቡን ተጋላጭነት ለመከላከል የባለሃብቶች ድጋፍ በየደረጃው ተጠናክሮ እንዲቀጥል አመራሩ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባም አሳስበዋል።

ለዚህም በቀጣይ ለሚከናወነው ሃብት የማፈላለጉ ስራ ትኩረት የሚሰጥባቸው ዘርፎች ተለይተው ወደስራ መገባቱንም አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም