ቀጥታ፡

በለይቶ ማቆያ የነበሩ ከውጭ የገቡ 500 ሰዎች ጤንነታቸው ተረጋግጦ ወጡ

መተማ ፣ሚያዚያ 18/2012 (ኢዜአ) በምዕራብ ጎንደር ዞን ከሱዳን ወደ ኢትዮጰያ የገቡና በለይቶ ማቆያ የነበሩ 500 ሰዎች ከከሮና ቫይረስ ነፃ መሆናቸው ተረጋግጦ ወደ ማህበረሰቡ መቀላቀላቸውን የዞኑ ኮሮና መከላከል ግብረ ኃይል አስታወቀ።

የግብረ ኃይሉ ፀሐፊና የዞኑ ማህበራዊ ልማት መምሪያ ኃላፊ ሲስተር ክሽን ወልዴ ለኢዜአ እንደተናገሩት በህጋዊም ሆነ በህገ ወጥ መንገድ ወደ ሃገራቸው የሚመለሱ ዜጎችም በፀጥታ ሃይሉ ጥብቅ ክትትል እየተደረገ ነው።

በዚህም ከሱዳን በቀጥታ በሚያዋሰኑ በዞኑ ቋራ፣ምዕራብ አርማጭሆና መተማ ወረዳዎች በተለዩ የመግቢያ በሮች እየተጠበቀ ነው ብለዋል።

እስካሁን በተደረገው ክትትልም  500 ግለሰቦች ተይዘው  በተዘጋጀው የለይቶ ማቆያ ከ14 ቀን በላይ ባሳለፉበት ወቅት  ከበሽታው ነፃ መሆናቸው ተረጋግጦ ወደ ማህበረሰቡ እንዲቀላቀሉ መደረጉን  አስታውቀዋል።

በአሁኑ ወቅትም ስምንት ግለሰቦች ከሱዳን ወደ ሀገር ውስጥ ሲገቡ ተገኝተው በለይቶ ማቆያ ሆነው ክትትል እየተደረገላቸው እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።

ቀደም ሲል በገንዳ ውኃና ምዕራብ አርማጭሆ ከነበረው በተጨማሪ በቋራ ወረዳና መተማ ዮሐንስ ከተማ አስተዳደር የለይቶ ማቆያ  ቦታ መዘጋጀቱን አመልክተዋል።

ዞኑን የሚያዋስነው የሱዳን ድንበር ሰፊ በመሆኑ የክትትል ስራውን አስቸጋሪ እንዳደረገው ጠቅሰው፤ ማህበረሰቡ በህገ ወጥ መንገድ የሚገቡ ግለሰቦችን ለፀጥታ መዋቅሩ በመጠቆም በሽታውን በመከላከል የድርሻውን እንዲወጣም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የመተማ ዮሃንስ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ገነት አደራጀው በሰጡት አስተያየት  በህገወጥ መንገድ ከውጭ  የሚገቡ አካላትን በመጠቆም የድርሻቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።

አሁንም ድረስ ከሱዳን ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ የኮንትሮባንድ እቃዎች እንደሚመለከት የጠቆመው ደግሞ

የገንዳ ውኃ ከተማ ነዋሪ ወጣት ሱራፌል እያዩ ነው።

በህገ ወጥ ንግድ እንቅስቃሴው የቫይረሱ ስርጭት መስፋፋት ስጋት እንዳለበት ጠቅሶ እራሱን ከበሽታው በመጠበቅ ለመከላከል የበኩሉን ጥረት እንደሚያደርግም ገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም