በሀድያ ዞን ኮሮናን ከመከላከል አንጻር መዘናጋት እንዳለ ተመለከተ - ኢዜአ አማርኛ
በሀድያ ዞን ኮሮናን ከመከላከል አንጻር መዘናጋት እንዳለ ተመለከተ
ሆሳዕና፣ ሚያዚያ 18/2012 ( ኢዜአ) የኮሮና ቫይረስን ከመከላከል አንጻር በህብረተሰቡ ዘንድ መዘናጋትና ቸልተኝነት እንዳለ ተመለከተ።
በሆሳዕና ከተማ የቤቴል ቀበሌ ነዋሪ አቶ ጥላሁን ድልነሳው እንዳሉት በሀገሪቱ የበሽታው ክስተትን ተከትሎ በጤና ባለሙያዎች የተሰጠውን ምክር በመቀበል ከቤታቸው መውጣት አቁመዋል።
ወረርሽኙን ለመከላከል ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ ለራስም ሆነ ለወገን ጠቃሚ በመሆኑ ከመንግስት በኩል የሚወርዱ አቅጣጫዎችን ተግባራዊ በማድረግ ለማገዝ ትኩረት መስጠታቸውን ተናግረዋል።
ሆኖም በከተማው ህብረተሰብ ከባለሙያ የሚሰጠውን ምክር ባለመስማትና መንግስት ያወጣውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ባለመፈጸም ክፍተት እንዳለ አመልክተዋል።
ይህም ለወገንም ሆነ ለሀገር ስለማይበጅ በመዘናጋት ጉዳት ከደረሰባቸው ሌሎች ሀገራት ትምህርት ተወስዶ ጥንቃቄ ልናደርግ ይገባል ብለዋል።
በከተማው የሴች ዱና ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ ወጋየሁ ታደሰ በበኩላቸው ወረርሽኙን ለመከላከል በህብረተሰቡ ዘንድ የጥንቃቄ መልዕክቶችን በመተግበር ረገድ ቸልተኝነት መኖሩን ጠቁመዋል።
ኮሮናን መቆጣጠር ለተወሰኑ አካላት ብቻ ሊተው የማይገባ በመሆኑ ተባብሮ በመስራት ሁሉም የመፍትሄ አካል ሊሆን እንደሚገባ አመልክተዋል።
"ህብረተሰቡ ሁሉም ነገር እንደ ቀድሞው ጤናማ የሆነ ያህል መዘናጋት ይታይበታል" ያሉት ደግሞ በሌሞ ወረዳ መሰና የባቆ ቀበሌ አርሶ አደር ኤርኬኖ ሀንዲኖ ናቸው።
መዘናጋቱን ሊለወጥ የሚችለው መንግስት ያወጣውን አዋጅ በተገቢው መንገድ ማስፈጸም ሲችል መሆኑን አመልክተዋል።
የዞኑ ጤና መምሪያ ኃላፊና የኮሮና መከላከል ግብረ ኃይል አባል አቶ ተመስገን ኃይሌ እንደገለጹት በአካባቢው በሽታውን ለመቆጣጠር የተለያዩ ስራዎች እየተከናወኑ ነው።
ይህም ሆኖ በህብረተሰቡ ዘንድ ቫይረሱን ከመከላከል አንጻር ቸልተኝነት እንደሚስተዋል አመልክተው
ክፍተቶችን በመለየት ግንዛቤ ለማስጨበጥ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አተገባበር ዙሪያ ያለውን ጉድለት ለማስተካከል ከጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።