ህግ የጣሱ አሽከርካሪዎች እርምጃ ተወሰደባቸው - ኢዜአ አማርኛ
ህግ የጣሱ አሽከርካሪዎች እርምጃ ተወሰደባቸው
ሰቆጣ፣ ሚያዚያ 18/2012 ( ኢዜአ ) በዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተላልፈው በተገኙ 51 አሽከርካሪዎች ላይ እርምጃ መውሰዱን የብሄረሰብ አስተዳደሩ የኮሮና መከላከል ግብረ ኃይል አስታወቀ።
የግብረ ኃይሉ አባልና የዞኑ መንገድ እና ትራንስፖርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ሰለሞን እሸቱ ለኢዜአ እንደገለፁት አሽከርካሪዎቹ እርምጃው የተወሰደባቸው የደረቅ ጭነት ብቻ ለመጫን የተፈቀደላቸውን በመጣስ የህዝብ ጭነት አገልግሎት ሲሰጡ ተደርሶባቸው ነው።
ለህዝብ ማመላለሻ አገልግሎት የዋሉት አይሱዙ፣ ኤፍ ኤስ አር እና ሲኖ ትራክ የተባሉ የጭነት ተሽከርካሪዎች ናቸው።
እንዲሁም የህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች የመጫን አቅማቸውን በግማሽ ቀንሰው ያላሳፈሩ እና ሦስት አምቡላንሶች ህሙማንን ማጓጓዝ ሲገባቸው የህዝብ ጭነት አገልግሎት ሲሰጡ የተገኙትን ጨምሮ በአጠቃላይ ከ33 ሺህ ብር በሚበልጥ ገንዘብ መቀጣታቸውን አቶ ሰለሞን አመልክተዋል።
በተሸከርካሪዎች ላይ የተጣለው ገደብ ለአሽከርካሪዎች እና ለባለንብረቶች የግንዛቤ ትምህርት መሰጠቱን ጠቅሰው ቫይረሱን ለመከላከል በሚደረገው ጥረትም በሰቆጣ ከተማ መግቢያ በሮች ላይ የተሳፋሪዎችን የጉዞ ታሪክ በስም ዝርዝር እየተያዘ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ማህበረሰቡ ህግን የሚተላለፉ ተሸከርካሪዎች ላይ እያደረገ ያለው ጥቆማ የሚበረታታ መሆኑን ጠቅሰው፤ አሁንም በሌሊት ሰውን ጭነው የሚንቀሳቀሱ እንዳሉ እንደተደረሰበትና ተከታትሎ ለህግ ለማቅረብ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
በቀጣይም አሽከርካሪዎች የወጣውን ህግ ተላልፈው የሚገኙ አሽከርካሪዎም ከገንዘብ ቅጣት ባለፈ የእስር እርምጃ እንደሚወሰድባቸው የግብረ ኃይሉ አባል አስታውቀዋል።