ቀጥታ፡

በጋምቤላ ክልል ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመቆጣጠር ጥረት እየተደረገ ነው

ጋምቤላ፤ ሚያዚያ 18/2012 (ኢዜአ) በጋምቤላ ክልል የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ስጋት ይሆነውን ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውርና የስደተኞች ያልተገደበ እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር ጥረት እየተደረገ መሆኑን የክልሉ ኮሮና መከላከል ግብረ ኃይል ገለጸ።

የግብረ ኃይሉ ሰብሳቢና  የክልሉ የሰላምና ጸጥታ ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ ቶማስ ቱት እንደተናገሩት ክልሉ ሰፊ የድንበር ወሰን ያለው በመሆኑ ጥበቃ ከሚደረግባቸው የመግቢና የመውጫ በሮች ውጭ ሰዎች ይገባሉ ይወጣሉ።

ከስደተኞች ጋር በተያያዘም የድንበር ወሰኑ ቅርብና ሰፊ በመሆኑ የመግባትና የመወጣት ሁኔታዎች መኖራቸውን ገልጸዋል።

በዚህም ምክንያት በሽታውን ለመከላከል እየተደረገ ባለው ስራ ላይ ችግር መፍጠሩን  ተናግረዋል።

ግብረ ኃይሉ ከመግቢያና መውጫ በሮች ጥበቃ በተጨማሪ ለህዝብ ግንዛቤ በመፍጠር የሚወጡና የሚገቡ ሰዎችን ለመቆጣጠር ጥረት እያደረገ መሆኑን አስረድተዋል።

የስደተኞችን ያልተገደበ እንቅስቃሴ ለመግታትም ከስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ አስተዳደር ጋር በመሆን ላልተወሰነ ጊዜ እንዲገደብና በህገ ወጥ መንገድ ሲንቀሳቀሱ የተገኙትም ለይቶ ማቆያ እንዲገቡ ስምምነት ላይ መደረሱን አስታውቀዋል።

በሀገሪቱ የተላለፈውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን ተላልፈው በሚገኙ አካላት ላይ እርምጃ እንደሚወስድም አቶ ቶማስ ገልጸዋል።

የክልሉ ጤና ቢሮ  ምክትል ኃላፊና  የግብረ ኃይሉ አባል  ዶክተር ኡጁሉ ኡጁሉ በበኩላቸው የኮሮና ቫይረስ በሀገሪቱ መከሰቱ ከተሰማበት ጊዜ ጀምሮ እንደ ክልል በርካታ ስራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

"በተለይም የሙቀት ልየታ፣ የለይቶ ማቆያና የህክምና አገልግሎች መስጫ ማዕከላትን በሰው ኃይልና በቁሳቁስ በማደራጀትን  ረገድ የሚበረታቱ ተግባራት ተከናውነዋል "ብለዋል።

ሆኖም  በክልሉ ጠረፋማ አካባቢዎች ያለው የሰዎች ዝውውር  እና የስደተኞች ያልተገደበ እንቅስቃሴ  ቫይረሱ በአካባቢው ሊከሰት ይችላል የሚል  ስጋት መፍጠሩን አመልክተዋል።

በክልሉ ህብረተሰቡ አካላዊ ርቀትን በመጠበቅ በኩል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ድንጋጌን እያከበረ አለመሆኑንም ጠቁመዋል።

በሀገሪቱ የተላለፈው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማክበርና በማስከበር ረገድ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በቅንጅት ሊሰራ እንደሚገባም ዶክተር ኡጁሉ አሳስበዋል።

በሌላ በኩል በጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ የተቋቋመው የለይቶ ማቆያና የህክምና አገልግሎት መስጫ ማዕከል አስፈላጊውን ዝግጅት ማጠናቀቁን የማዕከሉ አስተባባሪ ዶክተር ፍሬህይወት ጌታቸው ገልጸዋል።

ማዕከሉ ከ80 በሚበልጡ ባለሙያዎች የተደራጀ፣  የለይቶ ማቆያና የህክምና አገልግሎት መስጫዎች  እንዳሉትም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም