ለቀናት የኤሌክትሪክ አገልግሎት መቋረጡ ችግር ፈጥሮብናል -- የአ/አ ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
ለቀናት የኤሌክትሪክ አገልግሎት መቋረጡ ችግር ፈጥሮብናል -- የአ/አ ነዋሪዎች

አዲስ አበባ ሚያዚያ 18/2012 (ኢዜአ) በአዲስ አበባ ከተማ ልዩ ስሙ ዘበኛ ሰፈር ነዋሪዎች ለአምስት ቀናት ያህል የኤሌክትሪክ አገልግሎት በመቋረጡ ምግብ ማብሰልን ጨምሮ የየእለት ተግባራቸውን ለመከወን መቸገራቸውን ለኢዜአ ባቀረቡት ቅሬታ አስታውቀዋል።
ነዋሪዎቹ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ባለመኖሩ ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ ለመከላከል በቤት ዋሉ የሚለውን መመሪያ መተግበር እንዳንችልና በቅርቡ ወዳለው የሚመለከተው አካል በየጊዜው እንድንመላለስ አስገድዶናል ነው ያሉት።
የኤሌክትሪክ አገልግሎት መቆራረጥ ችግር በአካባቢው በተደጋጋሚ እንደሚገጥማቸው የገለፁት ነዋሪዎቹ፤ አሁንም ለአምስት ቀናት የዘለቀው የኤሌክትሪክ አገልግሎት መቋረጥ ምግባቸውን አብስለው እንዳይመገቡ እንዳደረጋቸው ገልፀዋል።
ነዋሪዎቹ በተደጋጋሚ በአቅራቢያቸው ወዳለው የሚመለከተው አካል ቢመላለሱም 'ጠብቁ ይሰራል' ከሚል ምላሽ ውጪ መፍትሄ እንደሌለው አስረድተዋል።
''ራሳችንን ከኮሮና ለመጠበቅ ቤት ውስጥ ብንውልም በምን ኤሌክትሪክ ተጠቅመን እንመገብ መስራት ያሉብንን ስራዎችስ እንከውን'' ሲሉም ይጠይቃሉ።
ነዋሪዎቹ ከኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ ባሻገር የኤሌክትሪክ ኃይል በሚመጣበት ጊዜ በተፈጠረ የኃይል መዋዠቅ ሳቢያ ንብረቶቻቸው መበላሸቱንም ያስረዳሉ።
ነዋሪዎቹ በዘመናት ግልጋሎት የተበላው የእንጨት ምሰሶ በማርጀቱ እንዲቀየርላቸው ቢያመለክቱም በሌላ እንጨት ከመደገፍ ወጪ ሌላ መፍትሄ እንዳልተሰጠውም ተናግረዋል።
ምሰሶዎቹ ከቤት ጋር የተገናኙ የኤሌክትሪክ መስመሮቹም በጣሪያዎቻቸው ላይ ስለሚያልፉ 'አደጋ ይገጥመናል' የሚል ስጋት እንደተደቀነባቸውም አብራርተዋል።
''ምላሽ ያጣው ጥያቄያችን ይመለስልን መንግስት ይመልከተን ዘላቂ መፍትሄንም እንሻለን'' ነው ያሉት ነዋሪዎቹ።
የአዲስ አበባ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በበኩሉ ችግሩን ለመፍታት እንደሚሰራ ገልጿል።
የአገልግሎቱ የኮሙዩኒኬሽን ስራ አስኪያጅ አቶ በቀለ ክፍሌ እንዳሉት፤ የኃይል መቆራረጥ በሚከሰትባቸው አካባቢዎች ላይ ኃይል የማመጣጠን ስራ ይሰራል።
ችግሩ መፍትሄ እንዲያገኝም በአካባቢው ለሚገኙ የአገልግሎቱ ሰራተኞች እንደሚያሳውቁና የነዋሪዎቹ ጥያቄ ምላሽ እንደሚያገኝም ነው ያስረዱት።
በአገልግሎቱ የሃይል አቅርቦት ችግር የተነሳ ለተበላሹ ቁሳቁሶች የመበላሸታቸው መንስዔ በባለሙያዎች ተረጋገጦ የካሳ ክፍያ የሚፈጸም መሆኑን ገልፀዋል።
ብልሽቱ በውስጥ መስመር ዝርጋታ ችግር ሊፈጠር የሚችል በመሆኑም ኀብረተሰቡ የራሱን ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበት ነው ያስገነዘቡት።
''መስመር የሚዘረጋው በአለም አቀፍ መስፈርት መሰረት ከበር 50 ሴንቲ ሜትር በመራቅ በውጭ ቢሆንም ሰው ቤት እያስጠጋ እየሰራ ምሰሶ ቤት ውስጥ የምናገኝባቸው ቦታዎችም አሉ'' ያሉት አቶ በቀለ፤ መልሶ መስመሩን ወደውጪ ለማስወጣት ካስፈለገ ክፍያ ያስፈልገዋልና እሱን በመፈፀም ማስወጣት እንደሚቻል አመልክተዋል።
ለኤሌክትሪክ መቆራረጥ ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠትም በከተማ ውስጥ ላሉ ነባር አካባቢዎች ቅድሚያ በመስጠት ያረጁ መስመሮችን በኮንክሪትና በሽፍን ሽቦ የመልሶ ግንባታ መርሃግብር እየተከወነ መሆኑንም ተናግረዋል።