በጌዴኦ ዞን አዋጁን ጥሰው የተገኙ 58 ተሽከርካሪዎች ተቀጡ - ኢዜአ አማርኛ
በጌዴኦ ዞን አዋጁን ጥሰው የተገኙ 58 ተሽከርካሪዎች ተቀጡ
ዲላ ሚያዝያ 18/2012 (ኢዜአ) በጌዴኦ ዞን የአስቸካይ ጊዜ አዋጅ ድንጋጌዎችን ጥሰው የተገኙ 58 ተሽከርካሪዎች እንዲቀጡ መደረጉን የዞኑ ኮሮና መከላከልና መቆጣጠር ግብረ ኃይል አስታወቀ።
የግብረ ኃይሉ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ሳሙኤል ቦኮ ለኢዜአ እንደገለጹት የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት የወጣውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተግባራዊ እንዲሆን የቁጥጥር ስራ እየተካሄደ ነው።
እስካሁን በተደረገው ቁጥጥርም የአዋጁን የክልከላ ድንጋጌዎች ተላልፈው ትርፍ ጭነው በተገኙ በአራት የህዝብ ማመላለሻና ሶስት ባጃጅ አሽከርካሪዎች እያንዳንዳቸው በ5ሺህ ብር መቀጣታቸውን ተናግረዋል
51 ሞተር ብስክሌቶች ደግሞ እንዳይንቀሳቀሱ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አስረድተዋል።
ግብረ ኃይሉ የኮሮና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጥሰው በሚገኙ አካላት ላይ የሚወሰደው እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አቶ ሳሙኤል አስታውቀዋል።
በመንግስት ተቋማትና ህዝብ በሚበዛባቸው አከባቢዎች የእጅ መታጠቢያ ውሃና ሳሙና በስፋት ቢመቻችም ከመጠቀም አንጻር ያለው መዘናጋት ሊታረሙ እንደሚገባ ያሳሰቡት ደግሞ የግብረ ኃይሉ አባልና የጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ ፍቅሩ በዴቻ ናቸው።
የጤና ተቋማት የኮሮና ቫይረስን ከመከላከሉ በተጓዳኝ ሌሎች ተላላፊ በሽታዎችንም ለመከላከል በትኩረት መስራት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።
"ነፍሰጡር እናቶች በጤና ተቋም ብቻ መውለድ እንዲችሉ በልማት ቡድንና ጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች የሚደረገው የቅርብ ክትትል ተጠናክሮ መቀጥል አለበት "ብለዋል።