ህብረተሰቡ በኮሮና ዙሪያ ያለው ቸልተኝነት አሳሰቢ አሳሳቢ ነው.. .የደቡብ ክልል ስፖርት ኮሚሽን - ኢዜአ አማርኛ
ህብረተሰቡ በኮሮና ዙሪያ ያለው ቸልተኝነት አሳሰቢ አሳሳቢ ነው.. .የደቡብ ክልል ስፖርት ኮሚሽን
ሀዋሳ ፤ሚያዝያ 17/ 2012 (ኢዜአ)ህብረተሰቡ በኮሮና ቫይረስ ዙሪያ ያለው ቸልተኝነት ካልተሰበረ አሳሳቢ መሆኑን የደቡብ ክልል ስፖርት ኮሚሽን ገለጸ።
የክልሉ ብስክሌት ቡድን አባላት በኮሮና ዙሪያ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ተዘዋውረው የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት ለመስጠት ዛሬ ወደ ዲላ አቅንተዋል።
የቡድኑ አባላት እንቅስቃሴያቸውን ከሀዋሳ ሲጀምሩ የክልሉ ስፖርት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ብሩክ ቡናሮ እንዳሉት መንግስት በቫይረሱ ዙሪያ ህብረተሰብን ለማስተማር ጥረት ቢያደርግም በህዝቡ ዘንድ ቸልተኝነት እየበዛ መጥቷል።
በሀገሪቱ በአሁኑ ወቅት ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ በየቀኑ በመገናኛ ብዙሀን እየተገለጸና ህብረተሰቡ እየሰማ ችላ ያለበት ሁኔታ አሳሳቢ መሆኑንም ገልጸዋል።
በግብይት ስፍራና በሌሎችም አካባቢዎች ህብረተሰቡ ርቀቱን ጠብቆ ከንክኪ ለመራቅ የሚያደርገው ጥረት እየቀነሰ መምጣቱን ተናግረዋል።
በጎ ፈቃደኛ የብስክሌት ስፖርተኞች ተዘዋውረው ህብረተሰቡን ለማስተማር ባቀረቡት ሀሳብ መሰረት ኮሚሽኑ ከኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር የደቡብ ቅርንጫፍ ጋር በመተባበር በሁሉም ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች የትምህርት ጉዞው መዘጋጀቱን አስታውቀዋል።
በኢትዮጵያ ቀይመስቀል ማህበር የደቡብ ቅርንጫፍ ኃላፊና የክልሉ የኮሮና መከላከል ግብረ ኃይል የበጎ ፈቃደኞች አስተባባሪ አቶ ተሾመ ታከለ በበኩላቸው" ኮሮና ገዳይ ቫይረስ መሆኑ እየታወቀ መዘናጋትና ቸልተኝነት ዋጋ የሚያስከፍል ነው "ብለዋል።
ህብረተሰቡ በየአካባቢው በተቀመጡ የእጅ መታጠቢያ ስፍራዎች እጁን ይታጠብ የነበረው አሁን እየቀረና ወደ ተለምዶ ሁኔታ እየተመለሰ እንደመጣም አስረድተዋል።
በክልሉ ዕውቅና ያላቸውን ስፖርተኞችን በመጠቀም በበሽታው ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ቅስቀሳ እየተደረገ እንደሚገኝ አውስተው እንቅስቃሴ የጀመሩት የብስክሌት ቡድን አባላትም አርአያ በመሆን ህዝቡን በማስተማር የድርሻቸውን እንዲወጡ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ከብስክሌተኞቹ መካከል ወጣት ምህረት ተስፋዬ እንዳለችው ህብረተሰቡ በቀላሉ እጁን በሳሙና በመታጠብ ራሱን ከቫይረሱ መከላከል እንደሚችል በሚንቀሳቀሱባቸው አካባቢዎች ለማስተማር ዝግጁ መሆኗን ተናግራለች።
ሌላዋ ብስክሌተኛ ወጣት ፀሐይ ማርቆስ በበኩሏ በአሁኑ ወቅት የህብረተሰቡ መዘናጋት ትልቅ ስጋት እንደሆነና ይህን ለመለወጥ በጉዞው መሳተፏን ገልጻለች።
"የበሽታው መተላለፊያ መንገዶቹን በማስተማር ሰዎች አውቀው ራሳቸውን እንዲጠብቁ ለማድረግ እተጋለሁ " ያለው ደግሞ ሌላው የጉዞው ተሳታፊ ብስክሌተኛው ወጣት በረከት ዳልጋ ነው።
ስፖርት ኮሚሽኑ ከክልሉ ብስክሌት ፌዴሬሽን ጋር በመሆን " ኮቪድ -19 የግንዛቤ ማስጨበጫ የብስክሌት ቱር በደቡብ" በሚል የተዘጋጀ ነው።
ብስክሌተኞቹ የመጀመሪያ ጉዟቸውን ዛሬ ወደ ዲላ ሲያቀኑ በቀጣይ ቀናትም በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች በመንቀሳቀስ የግንዛቤ ማጎልበቻ ትምህርት እንደሚሰጡ ተገልጿል።