ቀጥታ፡

በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ወጪና ገቢ ንግድ ላይ ለተሰማሩ አካላት የየብስ ትራንስፖርት ቅናሽ ተደረገ

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 17/2012 (ኢዜአ) በማኑፋክቸሪንግ ኤክስፖርት ዘርፍ ተሰማርተው ምርታቸውን ወደ ውጭ አገር ለሚልኩ አምራቾች ነጻ እና ቅናሽ የትራንስፖርት አቅርቦት መመቻቸቱን የትራንስፖርት ሚኒስቴር አስታወቀ።

በደረቅ ወደብ አገልግሎትም ለአምራቾቹ ቅናሽ መደረጉ ተመልክቷል።


በማኑፋክቸሪንግ ኤክስፖርት ዘርፍ ለተሰማሩና ምርታቸውን ወደ ውጪ አገር ለሚልኩ አምራቾች ለሚልኩት ጭነት ከትራንስፖርትና ከደረቅ ወደብ አገልግሎት ጋር በተያያዘ የተደረገውን ቅናሽ አስመልክቶ ዛሬ መግለጫ ተሰጥቷል። 

የትራንስፖርት ሚኒስትሯ ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉን ከውድቀት ለመታደግ መንግስት የዘርፉ ተዋንያኖችን የሚያግዝ ውሳኔ አስተላልፏል።

"ድጋፉም በትራንስፖርትና በሎጂስቲክስ ዘርፍ የደረቅ ወደብ አገልግሎትን ማዕከል በማድረግ የሚሰጥ እንዲሆን ተወስኗል" ብለዋል።

በውሳኔው መሰረትም ከፈረንጆቹ ግንቦት አንድ ጀምሮ ከኢንዱስትሪ ፓርኮችና ከኤክስፖርት ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች የሚወጡትን ምርቶች ከሦስት እስክ አምስት ወራት እስከ ጅቡቲ ወደብ ነጻ የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት እንደሚሰጥ ተናግረዋል።

"በተጨማሪም ከሞጆ ደረቅ ወደብ ላይ በቡር ለሚጭኑ እንዲሁም በባቡር ለማይመቹ አካባቢዎች ለሚጫኑ የወጪ ዕቃዎች የወደብና የትራንስፖርት አገልግሎት ላይ ቅናሽ ተደርጓል" ነው ያሉት ሚኒስትሯ።

ይህውም የደረቅ ወደብ አገልግሎት ክፍያ በየትኛውም የጭነት አይነት በ50 በመቶ እንዲቀነስ መደረጉን ነው ያስረዱት።

እንደሚኒስትሯ ገለጻ ከሃዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ እስከ ሞጆ ደረቅ ወደብ ለሚጓጓዙ ጭነቶች የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ሦስት ተሽከርካሪዎችን መድቦ በ50 በመቶ ቅናሽ አገልግሎት እንዲሰጥም ተወስኗል።

ሌሎች በባቡር ለማጓጓዝ አመቺ ያልሆኑ ጭነቶችን ወደ ጂቡቲ የሚወስዱ የማኑፋክቸሪንግ ኩባንያዎች ከባህር ትራንስፖርትና ከትራንስፖርተሮች ጋር በመሆን በ50 በመቶ ቅናሽ እንዲያጓጉዙ ተወስኗልም ነው ያሉት።

ከጂቡቲ ወደ ተለያዩ የዓለም ክፍሎች ምርታቸውን ለመላክ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ለሚጠቀሙ ላኪ ደንበኞችም እስከ 73 በመቶ ቅናሽ እንዲደረግ ነው የተወሰነው።

የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሮባ መገርሳ በበኩላቸው "ድርጅቱ የልማት ድርጅት እንደመሆኑ መጠን የመጣውን ችግር ለማለፍ እየጣረ ይገኛል" ብለዋል።

ከዚህ በፊት ድርጅቱ ለዘርፉ ተዋናዮች ካደረገው ቅናሽ በተጨማሪ ይኼኛው ዳግም የተደረገ ቅናሽ መሆኑን ነው የገለጹት።

የተደረገው ቅናሽ እጅግ ጠቃሚ መሆኑን ያስታወሱት አቶ ሮባ፣ ለአብነትም አንድ ላኪ ከዚህ በፊት ወደቻይና ለአንድ ጭነት እስከ 3 መቶ ዶላር የሚከፍል ቢሆን አሁን በእጥፍ እንደሚቀንስለት ነው ያስረዱት።

"በዚህ ወቅት 43 ፉርጎ ያለው አንድ ባቡር 60 መኪኖች የሚያነሱትን በአንዴ የማንሳት አቅም አለው" ያሉት ደግሞ የአትዮ-ጂቡቲ ምድር ባቡር ትራንስፖርት አክሲዮን ማህበር ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ጥላሁን ሳርካ ናቸው።

ቀደም ሲልም ማህበሩ ወደ ውጪ ለሚልኩ በሃምሳ በመቶ ቅናሽ ያደርግ እንደነበር ያስታወሱት ዳይሬክተሩ የአሁኑ ውስኔም ለዘርፉ ተዋናዮች ትልቅ ዕድል መሆኑን ነው ያመለከቱት።

በተለይም በተለያዩ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ለሚገኙ ላኪዎች ትልቅ እድል የሚፈጥር በመሆኑ በዕድሉን እንዲጠቀሙበት ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም