የአዳማ ቆርቆሮ ፋብሪካ ኮሮናን ለመከላከል የገንዘብና ምግብ እህል ድጋፍ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
የአዳማ ቆርቆሮ ፋብሪካ ኮሮናን ለመከላከል የገንዘብና ምግብ እህል ድጋፍ አደረገ
አዳማ፤ ሚያዝያ 17/2012 (ኢዜአ) የአዳማ ቆርቆሮ ፋብሪካ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል የሚረዳ የገንዘብ እና ምግብ እህል ድጋፍ አደረገ።
የድጋፍ ርክክቡ ዛሬ በአዳማ ከተማ በተከናወነበት ወቅት የፋብሪካው ባለቤት አቶ አብዱልሃኪም ሙሐመድ ባደረጉት ንግግር "በሽታውን ለመከላከል በተደረገልን ሀገራዊ ጥሪ መሰረት ድጋፍ አድርገናል" ብለዋል።
ህዝብ ከሌለ ሀብቱም ከንቱ ነው ያሉት አቶ አብዱልሃኪም፤ በሀገር ላይ የመጣውን አደጋ ለመቀልበስ የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ ለኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት 5 ሚሊዮን ብር በጥሬ ገንዘብ ማስረከባቸውን አስታውቀዋል።
በተጨማሪም በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ 2ሺህ 500 ወገኖች የሚውል ግምታቸው ከአምስት ሚሊዮን 500ሺህ ብር በላይ የሆኑ የማካሮኒ፣ዳቦ ዱቄት፣ዘይትና ሌሎች የምግብ እህል ዛሬ ለአዳማ ከተማ አስተዳደር አስረክበዋል።
እንዲሁም ባለሃብቱ ለዘጠኙ ክልሎችና ሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች ለእያንዳንዳቸው 100ሺህ ብር ድጋፍ በአዳማ ከተማ አስተዳደር በኩል እንዲደርሳቸው ሰጥተዋል።
የአዳማ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የኮሮና መከላከል ግብረ ኃይል አባል አቶ ሙሐመድ ጉዮ የፋብሪካው ባለቤት በራሳቸው ተነሳሽነት ላደረጉት ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ግብረ ኃይሉ እስካሁን ከ36 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የገንዘብና ቁሳቁስ ድጋፍ መሰባሰቡን አስታውሰው የአዳማ ከተማ ባለሃብቶች የጀመሩትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ከዚህም ሌላ የፋብሪካው ባለቤት ለአርሲ ዞን ሄጦሳ ወረዳ ግማሽ ሚሊዮን ብር የሚገመት የምግብ እህልና ዘይት ማበርከታቸውን የገለጹት ደግሞ ድጋፉን ለመረከብ አዳማ የተገኙት የሄጦሳ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ሙሐመድ አብዶ ናቸው። ለተደረገላቸው ድጋፍም ምስጋና አቅርበዋል።