ጉባኤው በአራት ኪሎ ዩኒቨርሲቲ ማቆያ ለሚገኙ ከስደት ተመላሾች የንጽህና መጠበቂያ ድጋፍ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
ጉባኤው በአራት ኪሎ ዩኒቨርሲቲ ማቆያ ለሚገኙ ከስደት ተመላሾች የንጽህና መጠበቂያ ድጋፍ አደረገ
አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 17/2012 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ከኖርዌይ የሃይማኖት ተራድኦ ድርጅት ጋር በመተባበር በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አራት ኪሎ ካምፓስ በተዘጋጀ ለይቶ ማቆያ ውስጥ ለሚገኙ ከስደት ተመላሾች የንጽህና መጠበቂያ ድጋፍ አደርገ።
ጉባኤው ቀደም ሲል ሲያደርጋቸው ከነበሩ ድጋፎች በተጨማሪ በዛሬው ዕለት 5 ሺህ ሊትር የንጽህና መጠበቂያ አልኮል ድጋፍ ያደረገው ከሳዑዲ አረቢያና ከጅቡቲ ለተመለሱ የስደት ተመላሾች ነው።
ድጋፉ በዩኒቨርሲቲው አራት ኪሎ ግቢ ውስጥ የሚገኙ ከ400 በላይ ከሳዑዲ አረቢያና ከጅቡቲ ስደት ተመላሾች በማቆያው ለ14 ቀናት ሲቆዩ ንጽህናቸውን ለመጠበቅ የሚያገለግል ነው።
የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ፀሐፊ ቀሲስ ሊቀ ትጉሀን ታጋይ ታደለ የሃይማኖት ተቋማት የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት የተለያዩ የድጋፍ ሥራዎችን እያከናወኑ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያን ጨምሮ ዓለምን እያስጨነቀ ካለው የኮሮናቫይረስ ፈጣሪ እንዲጠብቅ ሁሉም ሰው በየእምነቱ ተግቶ ሊጸልይ እንደሚገባም አመልክተዋል።
ለስደት ተመላሾቹ 5ሺህ ሊትር አልኮል ድጋፍ መደረጉን የገለጹት ቀሲስ ሊቀ ትጉሀን ታጋይ፤ የተደረገው ድጋፍ ውጤት እንዲያመጣ ህብረተሰቡ ተባባሪ መሆን እንዳለበት አመልክተዋል።
"በተለይ የጤና ባለሙያዎች በየጊዜው የሚመክሩትንና መንግስት የሚያወጣቸውን መመሪያዎች ህብረተሰቡ በትክክል ሰምቶ መተግበር ይገባል" ብለዋል።
በድጋፉ የርክክብ ስነስርአት ላይ የተገኙት የጤና ሚኒስትር ዴኤታዋ ወይዘሮ ሳህርላህ አብዱላህ በበኩላቸው የሃይማኖት ቋማት የኮሮናቫይርስን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት በተለያየ መንገድ ለመደገፍ እያደረጉት ላለው አስተዋጽም አመስግነዋል።
በዛሬው ዕለት ለስደት ተመላሾቹ የተደረገው የአልኮል ድጋፍ እጅን መታጠብ የማይቻልበት ሁኔታ ሲገጥም የኮሮናቫይርስን ለመከላከል የሚያግዝ መሆኑን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ከኖርዌይ የሃይማኖት ተራድኦ ድርጅት ጋር በመተባበር ያደረጉትን ድጋፍ የተረከቡት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተፈጠሮ ሳይንስ ፕሬዚዳንት ዶክተር አዲስዓለም አባተ ናቸው።
በድጋፍ የተረከቡትን አልኮል እንደግብአት ተጠቅመው የእጅ ንጽህና መጠበቂያ (ሳኒታይዘር) በማምረት ለአገልግሎት እንደሚያበቁም ተናግረዋል።