በምስራቅ ጎጃም ከ432 ሺህ በላይ የማህበረሰብ ክፍሎች አማራጭ የኃይል ምንጮች ተጠቃሚ ሆኑ - ኢዜአ አማርኛ
በምስራቅ ጎጃም ከ432 ሺህ በላይ የማህበረሰብ ክፍሎች አማራጭ የኃይል ምንጮች ተጠቃሚ ሆኑ
ደብረ ማርቆስ ሰኔ 26/2010 ምስራቅ ጎጃም ውስጥ እየተገባደደ ባለው የበጀት ዓመት ከ432 ሺህ በላይ የማህበረሰብ ክፍሎች አማራጭ የኃይል ምንጮች ለተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን የዞኑ ውሃ ፣መስኖና ኢነርጅ ልማት መምሪያ አስታወቀ። በበጀት ዓመቱ የተጠቃሚዎችን ፍላጎት መሰረት ያደረገ የኃይል አማራጮችን ማቅረብ ተችሏል፡፡ በመምሪያው የአማራጭ ኢነርጅ ቡድን መሪ አቶ አንበሉ መሰሉ ለኢዜአ እንስታወቁት ህብረተሰቡ በአገልግሎቱ ለመጠቀም ፍላጎት እያደገ በመምጣቱም ለማሰራጨት ከታቀደው 70 ሺህ በላይ የኃይል አማራጮች ማከናወን ተችሏል። የተሰራጩት የኃይል አማራጮች ከ51 ሺህ ማገዶ ቆጣቢ ምድጃ፣ 35 ሺህ በፀሃይ ኃይል የሚሰሩ ሶላሮችና 440 የሚሆኑት ደግሞ የባዮ ጋዝ ቴክኖሎጂዎች ናቸው። በተሰራጩት የኃይል አመራጮችም ከ432 ሺህ በላይ የቤተሰብ አባላት ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ቡድን መሪው ገልጸው አገልግሎቱ የቀረበውም በተመጣጣኝ ዋጋ እጅ በእጅ ክፍያና በብድር መሆኑን ጠቁመዋል። በዚህም ህብረተሰቡ ለማገዶ ፣ ለጋዝና ለመሳሳሉት የሚያወጣውን ወጪ እንቂቆጥብ ከማስቻሉም በላይ እየተመናመነ ባለው የደን ሃብት ላይ የሚደርሰውን ጫና ለመቀነስ ማገዙን አቶ አንበሉ ጠቅሰዋል። ከተጠቃሚች መካከልም በጎዛምን ወረዳ የአባሊባኖስ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ተሻለ አታለይ አንዱ ናቸው፡፡ በመኖሪያ ቤታቸው አቅራቢያ በተዘጋጀው የባዮ ጋዝ ቴክኖሎጂ የመብራት ኃይል ተጠቃሚ መሆናቸውን በሰጡት አስተያየት ተናግረዋል፡፡ በዚህም ቀደም ሲል ለኩራዝ በወር እስከ 90 ብር ድረስ ያወጡት የነበረውን ወጪ መቀነስ ከመቻላቸውም ሌላ ለምግብ ማብሰያም በመጠቀም ኑሮቸውን ለማሻሻል እንደረዳቸው ተናግረዋል። በዚሁ ወረዳ የጥጃን ቀበሌ ነዋሪ አቶ ይርዳው ታረቀኝ በበኩላቸው በፀሐይ ኃይል የሚሰራ የኃይል ምንጭ በማግኘታቸው ለጤና ችግር ሆናባቸው ከቆየው የኩራዝ ጭስ መላቀቃቸውን ገልጸዋል፡፡ አሁን መብራት እንደልብ እያገኙ ተማሪ ልጆቻቸው በአግባቡ በለሊት እንዲያጠኑና ውጤታማ እንዲሆኑ ምቹ ሁኔታ እንደተፈጠረላቸው ጠቅሰው ቀደም ሲል ለኃይል አቅርቦት በወር እስከ 200 ብር ያወጡ የነበረው እንዳስቀረላቸው ነው ያመለከቱት። በምስራቅ ጎጃም ባለፉት ዓመታትም ከ700 ሺህ በላይ አማራጭ የኃይል ምንጮችን ለህብረተሰቡ በማድረስ ተጠቃሚ መሆናቸውን ከውሃ ፣መስኖና ኢነርጅ ልማት መምሪያው የተገኘው መረጃ ያስረዳል።