የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ለደንበኞቹ ጠቃሚና መፍትሄ የያዙ ውሳኔዎችን አሳለፈ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ለደንበኞቹ ጠቃሚና መፍትሄ የያዙ ውሳኔዎችን አሳለፈ
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 17/2012( ኢዜአ) የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ደንበኞቹ ላጋጠማቸው የምርት መስተጓጎልና የገበያ ችግር መፍትኤ የሚሰጡ ውሳኔዎችን አሳለፈ።
በአለም አቀፍ ደረጃ በተከሰተው የኮቪድ19 ወረሽኝ ምክንያት የአውሮፕላን በረራ በመቋረጡ በፕሮጀክቶች ምርትና በገበያ ላይ ከፍተኛ መስተጓጎል እንደደረሰባቸው ባልኩ ለኢዜአ በላከው መግለጫ ገልጿል።
ለምርታቸው ግብአት ጥሬ እቃ ከውጭ የሚያስገቡና አምርተው ለመሸጥ ያልቻሉ እንዲሁም ምርታቸው በወቅቱ ለገበያ ባለመቅረቡ ለብልሽት ተዳርገው የተወገደባቸው በባንኩ ፋይናንስ የተቋቋሙ ፕሮጀክቶች የችግሩ ገፈት ቀማሽ እንደሆኑም ተጠቅሷል።
የባንኩ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ እንደየ ፕሮጀክቶቹ ባህሪ መደገፍ በሚገባቸው መጠን እንዲደገፉና ይህን አስቸጋሪ ጊዜ እንዲያልፉ ውሳኔዎችን አሳልፏል።
ውሳኔዎቹም የብድር ክፍያ ጊዜን ማራዘም፣ በብድር ላይ የሚሰላውን ወለድ ለተወሰነ ጊዜ ማንሳት፣ የLC ጊዜ ማራዘምና የLC ማራዘሚያ የአገልግሎት ክፍያን ማንሳት ናቸው።
ከዚህ ባለፈም ምርታቸውን ለውጭ ገበያ የሚልኩ እንደ አበባ አምራቾች ጉዳታቸው ታይቶ ከብድር ማራዘም በተጨማሪ ከወለድ ነጻ የሥራ ማስኬጃ ብድር እንዲሰጣቸው ውሳኔ ማሳለፉን ባንኩ በመግለጫው አስታውቋል።