የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለአቅመ ደካማ ዜጎች የምገባ መርሃ-ግብር ጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለአቅመ ደካማ ዜጎች የምገባ መርሃ-ግብር ጀመረ
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 17/2012 ( ኢዜአ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ አቅም ለሌላቸው ዜጎች በቀን አንድ ጊዜ የምገባ መርሀግብር መጀመሩን አስታወቀ።
የምገባ መርሀግብሩ ለ15 ተከታታይ ቀናት የሚካሄድ ሲሆን በእዚህም በቦሌ ክፍለ ከተማ በተለምዶ ''ቦሌ ቡልቡላ'' በሚባለው አካባቢ በተሰራው መጠለያ ጣቢያ የሚገኙና ምንም አይነት ገቢ የሌላቸው 400 የሚሆኑ ዜጎች ተጠቃሚ ይሆናሉ።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም ባደረጉት ንግግር ወቅቱ አስቸጋሪ በመሆኑና ለወገን ደራሽ ወገን በመሆኑ የምገባ መርሃ ግብሩ መጀመሩን ተናግረዋል።
"የኢትዮጵያ አየር መንገድ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ፈታኝ ሁኔታ ውስጥ ቢገኝም ወገኖቹን ከመታደግ ወደኋላ አይልም" ብለዋል።
በቀጣይም አየር መንገዱ ተመሳሳይ ሰብአዊ እርዳታዎችን እንሚያደርግ የገለጹት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ ''ይህን ወቅት ልናልፈው የምንችለው በመተባበር ብቻ በመሆኑ ሁሉም በመደጋገፍ የድርሻውን ሊወጣ ይገባል" ብለዋል።
የቦሌ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጥላሁን ፍቃዱ በእዚህ አስቸጋሪ ወቅት አየር መንገዱ ለዜጎች ላደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።
"እንደዚህ አይነት ሰዎችን ስትረዱ ለእናንተም ለመንፈሳዊ እርካታችሁም ትልቅ ቦታ ይኖረዋል" ያሉት ዋና ስራ አስፈጻሚው፤" ለተደረገው ድጋፍ ትልቅ ምስጋና ይገባችኋል" ሲሉም ተናግረዋል።
አቶ ጥላሁን ሌሎች ተቋማትም የአየር መንገዱን ፈለግ በመከተል ሰብዓዊ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
አየር መንገዱ ከምገባ መርሃግብሩ ባለፈ የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስም አበርክቷል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአሁኑ ወቅት የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል የሚያገለግሉ በጃክማ ፋውንዴሽን በኩል በእርዳታ የተሰጡ የህክምና ቁሶችን ወደ 51 የአፍሪካ አገራት በጥቂት ቀናት ውስጥ በማድረስ አህጉራዊ ኃላፊነቱን ጭምር እየተወጣ መሆኑን ተመልክቷል።