በኢትዮጵያ በየአካባቢው ያሉ የማህበረሰብ መሪዎች የኮቪድ-19 መከላከል ጥረቱን እያገዙ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ በየአካባቢው ያሉ የማህበረሰብ መሪዎች የኮቪድ-19 መከላከል ጥረቱን እያገዙ ነው
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 17/2012(ኢዜአ) በኢትዮጵያ በየአካባቢው ያሉ የማህበረሰብ መሪዎች ስለ ኮቪድ-19 መረጃ በመስተጠትና ግንዛቤ በማስጨበጥ የመከላከል ጥረቱን እያገዙ መሆኑን የዓለም ዓቀፉ የስደተኞች ድርጅት አስታወቀ።
የዓለም ዓቀፉ የስደተኞች ድርጅት (አይ.ኦ.ኤም) በየአካባቢው ያሉ የማህበረሰብ መሪዎችን በማስተባበር የበሽታውን ስርጭት ለመከላከል እየሰራ መሆኑን ገልጿል።
በዚህም የቫይረሱን ስርጭት አስመልክቶ የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራዎችን እየሰራ መሆኑን ነው ድርጅቱ ለኢዜአ በላከው መግለጫ ያስታወቀው።
በአፍሪካ አህጉር ከፍተኛ የስደተኛ ቁጥር ያላት ኢትዮጵያ በርከት ያሉ ሰዎች በኮሮናቫይረስ ከተያዙባቸው የአፍሪካ አገሮች መካከልም ትመደባለች።
በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሆነው አገር ለማቋረጥ ጥረት ሲያደርጉ በተደጋጋሚ ጊዜ ተስተውሏል ነው ያለው ድርጅቱ።
''በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ ማህበራዊ ርቀትን መጠበቅ ፈጽሞ የማይታሰብ ነው'' የሚሉት በድርጅቱ የኢትዮጵያ የስደት አስተዳደር ኃላፊ ማለምቦ ሞንጋ ናቸው።
እንደኃላፊው ገለጻ ሂደቱ ስደተኞችን ብቻ ሳይሆን ተቀባይ የህብረተሰብ ክፍሎችንም በከፍተኛ ሁኔታ ተጋላጭ የሚያደርግ ነው።
ይህን አደጋ ለመቀነስም 5 ሚሊዮን ሰዎችን መድረስ የሚችሉት የድርጅቱ 'የተግባቦት አስተባባሪዎች ' በተለይም ስድተኞችና ሌሎች ተጋላጭ የሕብረተሰብ ክፍሎች በቫይረሱ እንዳይጠቁ ለማድረግ እየሰሩ መሆኑን አመልክተዋል።
በቅርቡ ከ8 ሺህ በላይ ስደተኞች ከባህረ ሰላጤውና አካባቢው አገራት ወደኢትዮጵያ እንዲመለሱ መደረጉን በመግለጫው ያስታወሰው ድርጅቱ፣ ''ከስደተኞቹ መካከል ምናልባትም ለቫይረሱ ተጋላጭ የሆነ ሰው ሊኖር ይችላል'' ሲል ስጋቱን ገልጿል።
ይህንኑ ታሳቢ በማድረግ በድርጅቱ ድጋፍ በየአካባቢው ያሉ የማህበረሰብ መሪዎች ስደተኞች ባሉባቸው አካባቢዎች ተገኝተው ስለቫይረሱ መረጃ በመስጠት ላይ ናቸው ተብሏል።
ድርጅቱ ስለኮሮናቫይረሱ አደገኛነት ከሚሰጠው ስልጠና ጎን ለጎን ሰዎች ተሰደው ለቫይረሱ ተጋላጭ ከሚሆኑ ይልቅ በአካባቢያቸው አማራጭ የመተዳደሪያ መንገዶች ላይ እንዲያተኩሩ እያደረገ መሆኑም ተገልጿል።
ድርጅቱ በዚህ ወቅት እያደረገ ካለው የምግብ፣ የውሃና የንጽህና መጠበቂያ ቁሶች በተጨማሪ ስደተኞች ወደትውልድ ቄያቸው እንዲመለሱ ትራንስፖርት በማመቻቸት የኢትዮጵያን መንግስት እየደገፈ መሆኑን ኃላፊው አስረድተዋል።