ህዝቡ ኮሮናን ከመከላከል ጎን ለጎን የሕዳሴውን ግድብ ለማጠናቀቅ ድጋፉ እንደቀጠለ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ህዝቡ ኮሮናን ከመከላከል ጎን ለጎን የሕዳሴውን ግድብ ለማጠናቀቅ ድጋፉ እንደቀጠለ ነው
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 17/2012( ኢዜአ) ህዝቡ የኮሮናቫይረስን ለመመከት ከሚያደርገው ጥረት ባልተናነሰ የሕዳሴውን ግድብ ለማጠናቀቅ ድጋፉን መቀጠሉን ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ፅህፈት ቤት አስታወቀ።
የጽህፈት ቤቱ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሮማን ገብረስላሴ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳሉት የኮሮናቫይረስ በኢትዮጵያ ከተከሰተ በኋላ ብቻ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ በስጦታ ተለግሷል።
እንደ ዳይሬክተሯ ገለፃ በ8100A፣ በየክልሉና በየዞኑ የሚደረገው ድጋፍ፣ በባንክ በግል ቦንድ የሚገዙትንና የሚለግሱትን ሳይጨምር ለፌደራል ማስተባበሪያ ፅህፈት ቤት ድጋፋቸውን ካሳወቁት ብቻ የተለገሰው ከ14 ሚሊዮን ብር በላይ ደርሷል።
በተያዘው በጀት ዓመት ከሐምሌ እስከ መጋቢት ባሉት ወራት ከ530 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡንና ግድቡ ከተጀምረ ጀምሮ የተሰበሰበው ገንዘብም ከ13 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በላይ መሆኑን ጠቅሰዋል።
"በሕዳሴው ግድብ ግንባታና ውሃ አሞላል ጋር ተያይዞ ከግብፅ ጋር በሚደረገው ድርድር አሜሪካን ጨምሮ አንዳንድ ድርጅቶችና አገሮች የኢትዮጵያን ሉአላዊነት የሚነካ አቋም ማንፀባረቃቸው በኢትዮጵያዊያን ላይ ቁጭት በመፍጠር አዲስ ጉልበት ሆኗል" ሲሉም ወይዘሮ ሮማን ተናግረዋል።
የኮሮናቫይረስ ከመከሰቱ ጋር ተያይዞ ሰዎችን ሰብስቦና መድረኮችን ፈጥሮ መንቀስቀስ ስለማይቻል ህብረተሰቡ በቤቱ ሆኖ መረጃ የሚያገኝበትን አሰራር ለመዘርጋት እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
ከዚህ በተጨማሪ በውጭ ከሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር በቴክኖሎጂ መረጃ ለመለዋወጥ እንዲቻል የኢንተርኔትና የኢሜል ግንኙነቶች እንዲሁም የቪዲዮ ኮንፍረንሶች እየተካሄዱ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በቅርቡም በተለያዩ አገራት ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ምሁራን ጋር በተደረገ የቪዲዮ ኮንፍረንስ በግድቡ ዙሪያ ስላለው ውጫዊ ጫናና ይህንን ለመመከት በሚያስችሉ ምክረሀሳቦች ላይ ምክክር መደረጉንም ጠቅሰዋል።
በዚህም ኢትዮጵያ ፍትሃዊነትን ባማከለ መልኩ የዓባይን ወንዝ መጠቀሟን እንደምትቀጥል ስምምነት ላይ መደረሱን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያዊያንን ጥቅምና ሉአላዊነት በሚጋፉ ጉዳዮች ላይም ሁሉም ኢትዮጵያዊ በጋራ መቆም እንዳለበት የጋራ ውሳኔ ላይ መደረሱን ጠቅሰዋል።
"የኢትዮጵያ ህዝብ ዝቅተኛ ገቢ ካለው እስከ ሃብታም፤ ከተማረው እስካልተማረው፤ ከህፃን እስከ አዋቂ በአንድ ሆነን ግድቡን ወደማጠናቀቅ ደርሰናል" ያሉት ዳይሬክተሯ፣ በቀጣይ ቀሪውን 27 በመቶ የግንባታ ሥራ በድል እንዲጠናቀቅ ሁሉም የሚችለውን ድጋፍ እንዲያጠናከር ጥሪ አቅርበዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሥራ በአሁኑ ወቅት 73 በመቶ ላይ የደረሰ ሲሆን ግንባታው ከተጀመረ ጀምሮ ከህዝቡ የተሰበሰበው ገንዘብ ከ13 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በላይ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።