የአዋጁን የክልከላ ድንጋጌዎች ተላለፈው የተገኙ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች ላይ እርምጃ ተወሰደ - ኢዜአ አማርኛ
የአዋጁን የክልከላ ድንጋጌዎች ተላለፈው የተገኙ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች ላይ እርምጃ ተወሰደ
ፍቼ ሚያዝያ 16/2ዐ12 (ኢዜአ) ኮሮናን ለመከላከል በቅርቡ የወጣውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የክልከላ ድንጋጌዎችን ተላልፈው የተገኙ 247 የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች ላይ እርምጃ መውሰዱን በኦሮሚያ የሰሜን ሸዋ ዞን ትራንስፖርት ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡
የጽህፈት ቤቱ ኃላፊና የበሽታ መከላከል ግብረ ኃይል አባል አቶ ስዩም ከበደ ዛሬ እንደገለፁት እርምጃው የተወሰደው በአሽከርካሪዎችና ባለንብረቶች ላይ ነው።
አዋጁ በትራንስፖርት ዘርፍ ያስቀመጣቸውን ክልከላዎችና የጥንቃቄ ስራዎች በተመለከተ ወደ ስራ ከመገባቱ በፊት አስር ሺህ ከሚደርሱ ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ተደርጓል ብለዋል፡፡
ውይይቱ የተደረገው በዞኑ ካሉ የትረንስፖርት ማህበራት፣ አሽከርካሪዎችና ባለንብረቶች ጋር በሽታውን ለመከላከል መደረግ ባለበት አካላዊ ርቀትና ንፅህና ጋር ተያያዥ በሆኑ ጉዳዮች ዙሪያ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በዚህም መግባባት ላይ መደረሱን አመልክተዋል፡፡
ሆኖም በተለይ የገጠሩን ህብረተሰብ የመረጃ ክፍተት በመጠቀም ሰዎችን ደራርቦና አቀራርቦ መጫን፣ ከታሪፍ በላይ ማስከፈል፣ በሌሊት ከማጓጓዝ በተጨማሪ ለበሽታው ተጋላጭ የሆኑ ሁኔታዎችን ሲፈጥሩ መገኘታቸውን አስረድተዋል፡፡
በዚህም ከ1 ሺህ እስከ 3 ሺህ ብር ቅጣት እንዲሁም ከዘርፍ ውጭ የጭነት ተሽከርካሪን ለሰው ማጓጓዣ ያዋሉ አምስት ግለሰቦች እስከ 10 ሺህ ብር ቅጣት እንደተጣለባቸው አስታውቀዋል፡፡
በዞኑ የኤጀሬ ከተማ ነዋሪ አቶ መላኩ ወርዶፋ በሰጡት አስተያየተ በተለይም መለስተኛ የሕዝብ ማመላለሻ አይሱዙዎች ተገቢ ቁጥጥር ስለማይደረግባቸው አሳቻና ሰዋራ ስፍራዎችን በመምረጥ ከተገቢው በላይ ሰው በመጫንና ከታሪፍ በላይ እያስከፈሉ በመሆኑ ቁጥጥር ሊደረግባቸው ይገባል ብለዋል፡፡
ሌላው አስተያየት ሰጪ በያያ ጉለሌ ወረዳ የፍታል ቀበሌ ነዋሪ አቶ መገርሣ ሬባ አስር ብር ብቻ የነበረውን ከሶስት እጥፍ በላይ በማስከፈል እያጉላሉ ባሉ ላይ የእርምት እርምጃ እንዲወሰድ ጠይቀዋል፡፡
የፍቼ ከተማ ቀበሌ ዐ4 ነዋሪ ወይዘሮ ዝናሽ ግርማ በበኩላቸው በከተማ ውስጥ አንዳንድ አሽከርካሪዎች ከታሪፍ በላይ እንደሚያስከፍሉና ተጨማሪ ሰዎች የሚጭኑበት ሁኔታ ስለሚስተዋል አስፈላጊው ቁጥጥር እንዲደረግ ጠቁመዋል፡፡
በጅዳ ወረዳ የሚኒባስ አሽከርካሪው ወጣት ሰለሞን አልዩ በበኩሉ አሽከርካሪዎች ከነዳጅ፣ ከቀን ውሎ አበልና ፣ ከንግድ ስራ ግብር በተጨማሪ ለመለዋወጫ የሚያወጡትን ወጪ ያላገናዘበ ታሪፍ ቢወጣም በሽታውን በጋራ ለመከላከል ኃላፊነት እንዳለበት አምኖ ያለትርፍ እየሰራ መሆኑን ተናግሯል፡፡
የሰሜን ሸዋ ዞን ንግድ ጽህፈት ቤት ኃላፊና የግብረ ኃይሉ አባል አቶ ወርቁ ረጋሣ በበኩላቸው የተጠቀሱትን ችግሮች ለመከላከል የሚከታተሉ አካላት ቢኖሩም የህብረተሰቡ ድጋፍና እገዛ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል፡፡