ቀጥታ፡

በረመዳን ወቅት የኮሮናቫይረስ ተጋላጭነትን መቀነስ ይገባል

አዲስ አበባ ሚያዚያ 16/2012(ኢዜአ) ህዝበ ሙስሊሙ በረመዳን ወቅት ለኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) ተጋላጭ እንዳይሆን ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበት የኢትዮጵያ እስልምና ጠቅላይ ምክር ቤት አሳሰበ።

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ዋና ጸሃፊ ቃሲም መሃመድ ታጁዲን ''የረመዳ ወር እርስ በርስ የመተሳሰብና የመረዳዳት ወቅት ነው'' ብለዋል።

የረመዳን የጾም ጊዜ ከአምላክ ምህረት የሚለመንበት ወቅት መሆኑን ገልጸው፤ ለመላው ሙስሊም ኅብረተሰብ የ'እንኳን አደረሳችሁ' መልዕክት አድርሰዋል።

በረመዳን ወቅት የሙስሊሙ ኅብረተሰብ ለኮሮናቫይረስ ተጋላጭ ከሚያደርጉ ተግባራት መራቅ እንዳለበት አሳስበዋል።

በተለይም በኮሮናቫይረስ ምክንያት መስጂድ መስገድ መከልከሉን አስታውሰው፤ ''ይህንን ክልከላ አክብሮ ሌሎች መሰባሰቦችን ማስቀረት ይገባል'' ብለዋል።

በዚህ ረገድ ሙስሊሙ ኅብረተብ ላደረገው ትብብርና በጎ ተግባር ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ያም ሆኖ በዚህ ረመዳን ወቅት በተለይም በአንዳንድ ሥፍራዎች ተጠራርቶ የጀመዓ (ቡድን) ስግደትን ማቆም እንደሚገባ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ይህንንም ትዕዛዝ አልፎ በራስ ውሳኔ የጀመዓ ስግደት መፈጸም ከሼሪያ ሕግ ውጪ መሆኑን በመገንዘብ ኅዝበ ሙስሊሙ ትዕዛዙን እንዲያከብር ጠይቀዋል።

ሌሎችም በመንግሥትና በጤና ባለሙያዎች የሚተላለፉ ማሳሰቢያዎችና መልዕክቶችን በትክክል በመተግበር ሃላፊነትን መወጣት እንደሚገባ ዋና ጸሐፊው ገልጸዋል።

የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሠሃረላ አብዱላሂም ''በረመዳን ወቅት ከማንኛውን ራስን ለቫይረሱ ተጋላጭ ከሚያደርጉ ድርጊቶች መቆጠብ ይገባል' ብለዋል።

ያም ብቻ ሳይሆን ቫይረሱን ለመከላከል በጤና ባለሙያዎች የሚቀርቡትን ምክረ- ሃሳቦች ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባ መክረዋል።

''በተለይም እጅን በሳሙና አዘውትሮ መታጠብ፣ አካላዊ ርቀትን መጠበቅ እንዲሁም አስገዳጅ ካልሆነ በስተቀር በቤት ውስጥ መዋልን ሊከበሩ ይገባል'' ነው ያሉት።

በኢትዮጵያ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 117 የደረሰ ሲሆን ከበሽታው ያገገሙ ደግሞ 25 ደርሷል፤ እስካሁን ሦስት ሰዎች በቫይረሱ ምክንያት ለህልፈተ ህይወት ተዳርገዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም