ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ጋዝ ንግድ ስምምነት አደረገች

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 16/2012(ኢዜአ) ኢትዮጵያ 4 ትሪሊዮን ኪዩብ ጫማ የተፈጥሮ ጋዝ ማልማት የሚያስችል የተፈጥሮ ጋዝ ንግድ ስምምነት ከቻይና ኩባንያ ጋር ተፈራረመች።

ኢትዮጵያ ዛሬ ከተፈረመው የተፈጥሮ ጋዝ ንግድ ፕሮጀክት በቀጣዩ 20 አመታት 6 ቢሊዮን ዶላር እንደምታገኝ በጥናት ተረጋግጧል።

ስምምነቱን የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴርና ፖሊይ ጂሲኤል ፔትሮሊየም ኢንቨስትመንት ሃላፊነቱ የተወሰነ የቻይና ኩባንያ  አድርገዋል።

በኦጋዴን አካባቢ ከተገኘ አጠቃላይ 8 ትሪሊዮን ኪዩብ ጫማ የተፈጥሮ ጋዝ  ውስጥ 4 ትሪሊዮን ኪዩብ ጫማ ማልማት የሚያስችል ስምምነት ነው የተደረገው።

ስምምነቱ የተፈጥሮ ጋዝን በማልማት ለውጭና አገር ውስጥ ገበያ ማቅረብ የሚያስችል ሲሆን የአገር ውስጥ አቅርቦት ቅድሚያ ይሰጠዋል ተብሏል።

የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስትር ዶክተር ሳሙኤል ኡርቃቶ የተደረገው የተፈጥሮ ጋዝ ንግድ ስምምነት ለኢትዮጵያ ፋይዳው ከፍተኛ መሆኑን አብራርተዋል።

ለሚቀጥሉት 25 አመታት የሚቆየው ይህ ፕሮጀክት የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት፣ የስራ እድል በመፍጠርና ለኢንዱስትሪዎች ያለውን ጠቀሜታ አስረድተዋል።

ወቅቱ በኮሮናቫይረስ እየተፈተነ ቢሆንም ስራውን እውን ለማድረግ ርብርብ እንደሚደረግ ነው ሚኒስትሩ የገለጹት።

የፖሊይ ጂሲኤል ፔትሮሊየም ኢንቨስትመንት ሃላፊነቱ የተወሰነ ኩባንያ ዋና ዳይሬክተር ሊ ዌይ በበኩላቸው በስምምነቱ መሰረት ፕሮጀክቱ የተያዘለትን አላማ እንዲያሳካ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በትብብር እንደሚሰሩ ገልዋል።

ለአገር ውስጥና ለውጭ ገበያ ለማቅረብ የጋዝ ግዥና ሽያጭ እንዲሁም ሌሎች ስራዎችን ለማከናወን በቀጣይ ሌሎች ስምምነቶች እንደሚደረጉ ተገልጿል።

ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ጋዙ ከሚወጣበት ጀምሮ እስከ ጂቡቲ ጠረፍ በኢትዮጵያ መንግስትና ኩባንያው ይካሄዳል።

በኢትዮጵያ በነዳጅና ተፈጥሮ ጋዝ ዘርፍ ስድስት ቦታዎች ተለይተው በአራት ኩባንያዎች የነዳጅ ፍለጋና ምርት ስራ እያከናወኑ እንደሚገኝ የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም