ኮሮናን ለመከላከል 20 ሺህ የሚጠጋ ወጣቶች በበጎ ፍቃደኝነት ሥራ ተሰማርተዋል - ኢዜአ አማርኛ
ኮሮናን ለመከላከል 20 ሺህ የሚጠጋ ወጣቶች በበጎ ፍቃደኝነት ሥራ ተሰማርተዋል
አዲስ አበባ ሚያዚያ 16/2012(ኢዜአ) የኮሮናቫይረስን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት በአገር አቀፍ የወጣት ሊግ አደረጃጀት በኩል ቁጥራቸው 20 ሺህ የሚጠጋ ወጣቶች በበጎ ፍቃደኝነት ሥራ ላይ መሰማራታቸውን የኢትዮጵያ ወጣቶች ሰላምና ብልጽግና ተልዕኮ ሊግ ገለጸ።
የኢትዮጵያ ወጣቶች ሰላምና ብልጽግና ተልዕኮ ሊግ ፕሬዚዳንት አቶ ብርሃኑ በቀለ የኮሮናቫይረስን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ወጣቶች ከእጅ ንክኪ የሆኑ መታጠቢያዎችን ከማቅረብ ጀምሮ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ለአብነትም በአዲስ አበባ ፒያሳ ሚኒሊክ አደባባይ አካባቢ ከእጅ ንክኪ ነጻ በሆነ መልክ ከ400 ሺህ ብር በላይ በሆነ ወጪ የንጽህና መጠበቂያ መተከሉን ገልጸዋል።
በአሶሳ ከተማ ከእጅ ንክኪ ነፃ የሆኑ የእጅ መታጠቢያዎች በወጣቶች በኩል ተተክለው ለህብረተሰቡ አገልግሎት እየዋሉ መሆናቸውንም ተናገረዋል።
እንደ አገር የኮሮናቫይረስን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት በአደረጃጀቱ በኩል ቁጥራቸው 20 ሺህ የሚጠጋ ወጣቶች በበጎ ፍቃደኝት ሥራ ላይ መሰማራታቸውን አመልክተዋል።
"የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራው በተለይ የጤና ባለሙያ ሆነው የአደረጃጀቱ አባል በሆኑ ወጣቶች እየተሰራ ነው" ሲሉም ተናግረዋል ።
እንደ አቶ ብርሀኑ ገለጻ በተለያዩ የአገሪቱ ክልል የኮሮናቫይረስን ለመከላከል የሚረዱ ቁሶች አቅርቦት በሚፈለገው መጠን አይደለም።
በመሆኑም በቀጣይ ከአዲስ አበባ በተጨማሪ በክልሎች የቁሳቁስ አቅርቦት ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚገባ ነው የተናገሩት።
የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራው በበጎ ፍቃደኛ የጤና ባለሙያችም ጭምር እየተሰራ መሆኑን የጠቆሙት ደግሞ የኢትዮጵያ ወጣቶች ሰላምና ብልጸግና ተልጽኮ ሊግ የጤናው ዘርፍ አስተባባሪ ዶክተር ወይንአብ ደጉ ናቸው።
የጤና ባለሙያዎች የወጣቶች አባል በመሆን በትርፍ ጊዜያቸው የጀመሩትን የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራው አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጠይቀዋል።