የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እምነት ተከታዮች ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ ቀረበ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እምነት ተከታዮች ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ ቀረበ

አዲስ አበባ ሚያዚያ 16/2012 (ኢዜአ) በኮቪድ-19 በሽታ ምክንያት በገዳማትና አድባራት የሚገኙ አካላትን ከችግር ለመታደግ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ የሆኑ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እምነት ተከታዮች ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ ቀረበላቸው ።
የአዲስ አበባ አገረ ስብከት ዋና ስራ አስኪያጅና የአዲስ አበባ ኃይማኖት ተቋማት የቦርድ ሰብሳቢ መላከ ህይወት ቆሞስ አባ ኃይለ ገብርኤል ነጋሽ ምዕመኑ የአቅሙን እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።
''ምዕመናን መልካም ማድረግ ከበጎ አስተሳሰብና ስብዕና የሚመነጭ መሆኑን በመረዳት በበሽታው ምክንያት ለተጎዱና ቀን ለጎደለባቸው ሁሉ ድጋፍ ማድረግ ሞራላዊ ግዴታ ነው'' ብለዋል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመግታት ዓብይ ፆምንና አበይት በዓላትን ምዕመናን በቤታቸው ሆነው በጸሎት እንዲያሰልፉ ማድረጓንም አስታውሰዋል።
ይህ ውሳኔ በምዕመናን አስተዋጽኦ የሚገለገሉ ገዳማት፣ አድባራት፣ ካህናትና ቤተሰቦቻቸው ለከፋ አደጋ ተጋላጭ እንዲሆኑ ያደረጋቸው መሆኑን ጠቁመዋል።
በመሆኑም አገር ስብከቱ በሽታው ይወገድ ዘንድ ከሚያደርገው ጸሎት ጎን ለጎን ሙሉ ጊዜውን በመሰዋት ሊመጣ የሚችለውን ችግር ለመቅርፍ የሚያችል ዝግጅት እያደረገ ነው።
በዚሁ መሰረት ከአገረ ስብከትና ከአጥቢያ ቤተ ክርስትያናት የተዋቀረ ኮሚቴ በመሰየም ገንዘብና ደረቅ ምግቦችን ለመሰብሰብ ዝግጅት ማጠናቀቁን ገልጸዋል።
እንደ መላከ ህይወት ገለጻ፤ ድጋፍ ለማሰባሰብ በተመረጡ አብያተ ክርስቲያናት ምዕመኑ የደረቅ ምግብና የንጽህና መጠቂያ ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረግ ይችላሉ።
ምዕመኑ ይህን ጊዜ ማለፍ የሚችለው በጋራ በመረባረብ መሆኑን በመረዳት በንግድ ባንክ በተከፈተ ዝግ የሂሳብ ቁጥር 1000328711404 ገንዘብ ገቢ እንዲያደርጉም ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።
ይህንኑ ተግባር መምህራን፣ የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች፣ መንፈሳዊ ማህበራት ዓላማውን በማስተዋወቅና በማስተባበር እንዲተባበሩም ጥሪ አቅርበዋል።
ቤተክርስትያኗ ለበሽታው መከላከል ይውል ዘንድ ሶስት ሚሊዮን ብር ድጋፍና ትምህርት ቤቶቿን እንዲሁም ኮሌጆቿን ለለይቶ ማቆያነት መስጠቷ ይታወሳል።