ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን የኮሮናን ስርጭትን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት ድጋፍ አደረገች

አዲስ አበባ ሚያዚያ 16/2012 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን የኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) ስርጭትን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ የአንድ ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገች።

የኢትዮጵያው የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ጳጳስ ካርዲናል ብርሃነኢየሱስ እንደተናገሩት፤ ቤተክርስቲያኗ የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል የተለያየ ተግባር እያከናወነች ትገኛለች።

ቤተክርስቲያኗ ከጤና ሚኒስቴር የሚሰጠውን የጥንቃቄ መመሪያ በህብረተሰቡ እንዲተገበር የበኩሏን እየተወጣች እንደሆነም ገልጸዋል።

በቤተክርስቲያኗ የጤና ተቋም በኩል ለሚሰራው የወረርሽኙ መከላከል ስራ እገዛ እያደረጉ ለሚገኙ አካለት ምስጋናቸውን ያቀረቡት ካርዲናሉ፤ በመንግስት በኩል የሚደረገውን ጥረት ቤተክርስቲያኗ እንደምትደግፍ አረጋግጠዋል።

የቤተክርስቲያኗ ጠቅላይ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አባ ተሾመ ፍቅሬ በበኩላቸው የቤተክርስቲያኗ የጳጳሳት ጉባዔ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መከላከያ መመሪያ ወጥቶ የመከላከል ስራ እየተከናወነ እንደሆነ አመልክተዋል።

በቤተክርስቲያኗ የጤና ተቋማት በኩል በመላ አገሪቱ ስለኮሮናቫይረስ ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው፤ መንግስት የሚያወጣቸውን የመከላከል ርምጃዎች እየተተገበሩ እንደሆነ ጠቁመዋል።

በተለይም ውሃን ጨምሮ የተለያዩ የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶችና ግብዓቶች ከተለያዩ አካላት በተገኘ ድጋፍ ለጤና ተቋማቱና ለህብረተሰቡ እንዲደርስ መደረጉን ተናግረዋል።

ድጋፍን የተረከቡት የኮሮናቫይረስን ለመከላከል የተቋቋመው ብሔራዊ የድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ የሃብት አሰባሰብ ንዑስ ኮሚቴ ሰብሳቢ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ለድጋፉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ቤተክርስቲያኗ ዘር፣ ቀለምና ሃይማኖት ሳትለይ ድጋፍ ማድረጓ የተለመደ የዘወትር ተግባሯ እንደሆነ የገለጹት አምባሳደር ምስጋኑ፤ ለኮቪድ-19 መከላከል የምትሰራው ስራ የሚጠበቅ እንደሆነ አመልክተው አድናቆታቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ጳጳሳት ጉባኤ 
የኮሮና ቫይረስ ወረርሺኝን ለመከላከል ባወጣው መመሪያ የቤተክርስቲያን ኃላፊዎች ሐዋርያዊ አገልግሎትን ለማበርከት በመንግሥት የተላለፉ የጥንቃቄ እርምጃዎችን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችሉ አዳዲስ ሃሳቦችን ጭምር በማፍለቅ የመተባበር እና የመደገፍ የሞራል ግዴታ አለባቸው።

በካቶሊክ ቤተክርስቲያን ስር የሚሠሩ የጤና ተቋማት በሁሉም ደረጃ ከጤና ሚኒስቴር ጋር በቅርበትና በትብብር እንዲሠሩ የሚደረግ መሆኑን መመሪያው ያስቀምጣል።

እንዲሁም ተገቢውን ግንዛቤ ለማስጨበጥ፣ ማኅበራዊ እና የአመለካከት ለውጥ ለማምጣት ሕዝቡን ለማስተማር ጥረት እንዲደረግ መመሪያ ወጥቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም