ቀጥታ፡

ኮሮናን ለመከላከል ከ25 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ድጋፍ ተደረገ

አዲስ አበባ ሚያዚያ 16/2012 9 (ኢዜአ) የኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) ስርጭትን ለመከላከል የሚያግዝ ከ25 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ድጋፍ ማድረጉን የኢትዮጵያ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና ቴክኒክና ሙያ ተቋማት ማህበር አስታወቀ።

የትምህርት ክፍያ ''የወቅቱን ችግርና የቤተሰብ ሁኔታን በማገናዘብ በከፍተኛ የመግባባት ሥሜት ሊፈጸም ይገባልም'' ብሏል ማህበሩ። 

ማህበሩ የኮሮናቫይረስን ለመከላከል የሚያደርገውን ድጋፍና የተማሪዎች ክፍያ አስመልክቶ ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል።  

የማህበሩ የቦርድ ፕሬዚዳንት አቶ ሞላ ጸጋዬ "ወረርሽኙን ለመከላከል መንግስት ያቀረበውን የድጋፍ ጥሪ የማህበሩ አባላት እንዲቀላቀሉ እያስተባበሩ" መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም መሰረት አባላቱ በገንዘብና በአይነት አጠቃላይ ድምሩ 25 ሚሊዮን ብር የሚገመት ድጋፍ ማድረጋቸውን አንስተዋል።   

በገንዘብ ደረጃ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት 2 ሚሊዮን 760 ሺህ ብር ድጋፍ መደረጉን የጠቆሙት አቶ ሞላ ለዕቃ ማከማቻ የሚሆኑ 41 ህንጻዎች፣ ለለይቶ ማቆያ የሚሆኑ መሰብሰቢያ አዳራሾች፣ አልጋና ፍራሾች እንዲሁም 30 መኪናዎች ድጋፍ መደረጉን ተናግረዋል።

ማህበሩ በራሱ ለኮቪድ-19 መከላከያ 590 ሺህ ብር ድጋፍ ማድረጉንና በቀጣይም አስፈላጊውን እገዛ ለማበርከት ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።  

የማህበሩ ምክትል ፕሬዚዳንት ተባባሪ ፕሮፌሰር ወንድወሰን ታምራት በበኩላቸው "ካለፈው አንድ ወር ጀምሮ የትምህርት ክፍያ በመቋረጡ በተቋማቱ ላይ ችግር እያጋጠመ ነው" ይላሉ።

''ተቋማቱ ለኪራይ፣ ለብድር፣ ግብር እና ደመወዝ ለመክፈል ወጪ እያደረጉ ነው'' ያሉት ተባባሪ ፕሮፌሰሩ፤ በግሉ ዘርፍ ያሉት የትምህርት ተቋማት ሙሉ በሙሉ ወጪያቸውን የሚሸፍኑት ከተማሪዎች በሚሰበስቡት ገቢ በመሆኑ ሊታሰብበት እንደሚገባ አመላክተዋል።

''የማህበሩ ቦርድ የተማሪዎች ክፍያ ማቆም በተቋማቱ ህልውና ላይ ትልቅ ስጋት መደቀኑን በማመኑ ውሳኔ አሳልፏል'' በማለት ምክትል ፕሬዝዳንቱ ገልጸዋል።

በዚህም የተማሪዎች ክፍያ በስምምነት እንዲፈጸም ማድረግና የትምህርት ተቋማቱ በወርሃዊ ክፍያ ላይ ቢያንስ የ25 በመቶ ቅናሽ እንዲያደርጉ መወሰኑንም ጠቅሰዋል።  

በበሽታው ምክንያት በደረሰባቸው ቀጥተኛ ችግር ክፍያ መፈጸም ለማይችሉ ተማሪዎች ተቋማቱ ነጻ የትምህርት እድል እንዲሰጡ ቦርዱ መወሰኑን የተናገሩት ምክትል ፕሬዝዳንቱ፤ ''በወቅቱ መክፈል ላልቻሉ ደግሞ ያለ ቅጣት ክፍያ እንዲራዘም ተደርጓል'' ብለዋል።

በሌላ በኩል "መንግስት ለተቋማቱ የብድር አገልግሎት እንዲያመቻችና ከታክስ ጋር በተያያዘ ቅነሳ እንዲደረግ ማህበሩ ጥሪ ያቀርባል'' ብለዋል።

ማህበሩ የቤት ኪራይ ቅነሳዎችና ስረዛዎች እንዲበረታቱ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትብብር እንደሚሰራ አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም