የወልዲያ ዩኒቨርሲቲ እና ኢትዮ ስኳር አክሲዮን ማህበር የኮሮና መከላከያ ቁሳቁስ ድጋፍ አደረጉ - ኢዜአ አማርኛ
የወልዲያ ዩኒቨርሲቲ እና ኢትዮ ስኳር አክሲዮን ማህበር የኮሮና መከላከያ ቁሳቁስ ድጋፍ አደረጉ
ሰቆጣ/አዳማ ሚያዚያ16/2019 (ኢዜአ) የወልዲያ ዩኒቨርሲቲ እና ኢትዮ ስኳር አክሲዮን ማህበር ኮሮናን ለመከላከል የሚያግዝ የቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጋቸው ተገለጸ።
የወልዲያ ዩኒቨርሲቲ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ድጋፍ እያደረገ መሆኑን በዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ሱልጣን መሃመድ ተናግረዋል።
ከድጋፉ ውስጥ ትናንት ያበረከቱት 135 ሺህ ብር ግምት ያላቸው ፈሳሽ ሳሙና፣ የንጽህ መጠቂያ ሳኒታይዘር እና በሰቆጣ ከተማ ለተዘጋጀው የለይቶ ማከሚያ ማዕከል አገልግሎት የሚውሉ ግብአቶችን ጠቅሰዋል።
ዩኒቨርሲቲው የኮሮና ቫይረስን መመርመር የሚያስችል የላብራቶሪ ማዕከል ለማቋቋም እየተዘጋጀ መሆኑንም አስረድተዋል።
የዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር የኮሮና መከላከል ግብረኃይል ምክትል ሰብሳቢ አቶ ሞገስ መርካ የወልዲያ ዩኒቨርሲቲ ያደረገው የቁሳቁስ ድጋፍ በቅድመ መከላከል ስራው ይስተዋሉ የነበሩ ችግሮችን ለማቃለል እንደሚያግዝ በመግለጽ ምስጋናቸው አቅርበዋል።
"በድጋፍ የተገኙትን ግብዓቶችም ለታለመላቸው ዓላማ እንዲውል ክትትልና ቁጥጥር ይደረጋል" ብለዋል።
ቀደም ሲልም የወሎ ዩኒቨርሲቲ በሽታውን ለመከላከል የሚረዳ የተለያየ ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉንም አስታውሰዋል።
በሌላ በኩል የኢትዮ ስኳር አክሲዮን ማህበር በወንጂ ከተማና አካባቢው ለሚኖሩ ጡረተኞችና አረጋዊያን ድጋፍ ማድረጉን የማህበሩ ሥራ አስኪያጅ አቶ ብተው አለም ገልጸዋል።
ድጋፉ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል በተገደበው እንቅስቃሴ ጡረተኞችና አረጋዊያን ለጉዳት እንዳይጋለጡ ለማገዝ ነው ብለዋል።
በዚህም የዳቦ ዱቄትና ሌሎች ቁሳቁሶች 200 ለሚሆኑ አረጋዊያንና ጡረተኞች ድጋፍ ማድረጋቸውን አቶ ብተው ተናግረዋል።
ማህበሩ በቋሚነት በወንጂ ከተማና አካባቢዋ ለሚገኙ 100 ተማሪዎች በየዓመቱ ሙሉ የመማሪያ ቁሳቁስና አልባሳት ድጋፍ እየደረገ መሆኑን ጠቅሰው "በተጨማሪም 50 የሚሆኑ አረጋዊያን ቋሚ የገንዘብ ድጎማ እንሰጣለን "ብለዋል።
በከተማው የወንጂ ዓለም ጤና ቀበሌ ሊቀመንበር የኮሮና መከላከል ግብረ ኃይል ሰብሳቢ አቶ ብርሃኑ ሃተዑ የኢትዮ ስኳር አክስዮን ማህበር ለጡረተኞችና በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ የአካባቢው ነዋሪዎች ዱቄት፣ማካሮኒና የበቆሎ እህል ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል።
ማህበሩ በተጨማሪም የውሃ ማጠራቀሚያ ጋን (ሮቶ)፣ የእጅ ማስታጠቢያና የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች ማበርከቱንም አመልክተዋል።
ድጋፍ ከተደረገላቸው መካከል ወይዘሮ የሱነሽ ደረሰ በሰጡት አስተያየት " ካለንበት እድሜ አንፃር ተንቀሳቅሰን መስራት ባለመቻላችን በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ነው ያለነው "ብለዋል።
የተደረገላቸው የምግብና ቁሳቁስ ድጋፍ ችግራቸውን ለማቃለል እንደሚረዳቸው ተናግረዋል።