ቀጥታ፡

የሕዳሴ ግድብን ውሃ ለመሙላት የሚያስችል ዝግጅት እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 16/2012(ኢዜአ) ከመጪው ሐምሌ ወር ጀምሮ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ውሃ ለመሙላት የሚያስችል ቅድመ ዝግጅት እየተካሄደ መሆኑ ተገለጸ።

ከኢትዮጵያ የሕዳሴው ግድብ ተደራዳሪዎች ቡድን አባል ኢንጂነር ጌዲዮን አስፋው እንዳሉት በመጀመሪያው የግድቡ ውሃ ሙሌት ሥራ የሚሞላው የውሃ መጠን 4 ነጥብ 9 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሊትር ነው።

ይህም የግድቡን ሁለት ተርባይኖች ማንቀሳቀስ የሚያስችል ነው።

በሚቀጥለው ዓመትም 13 ነጥብ 5 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሊትር ውሃ ለግድቡ ይሞላል ተብሎ እንደሚጠበቅ ያመለከቱት ኢንጂነር ጌዲዮን፤ በአጠቃላይ የሚሞላው 18 ነጥብ 4 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሊትር ውሃ ሁሉንም የግድቡን ተርባይኖች ለማንቀሳቀስ እንደሚያስችል አስረድተዋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ ለኢዜአ እንዳሉት በአሁን ጊዜ የግድቡ ግንባታ ሥራ ተጠናክሮ ቀጥሏል።

ከመጪው ሐምሌ ወር ጀምሮ ግድቡ ውሃ መያዝ እንዲችልም ዝግጅት እየተደረገ ነው ብለዋል።

ከዝግጅት ሥራዎች መካከል 1 ሺህ ሄክታር በሚደረስ መሬት ላይ የሚከናወነው የደን ምንጣሮ ሥራ አንዱ ሲሆን ይህም በቤንሻንኩል ጉምዝ ክልል ሥራ አጥ ወጣቶች እንደሚከናወን ኢንጂነር ክፍሌ ተናግረዋል።

"በቀጣይ በሚከናወነው ተጨማሪ የደን ምንጣሮ ሥራ ከክልሉ አጎራባች አካባቢዎች የሚገኙ ሥራ አጥ ወጣቶች ይሳተፋሉ" ብለዋል።

ግብጽ የሕዳሴው ግድብ የውሃ ሙሌት ሥራ ከ12 እስከ 20 ዓመት እንዲሆን፣ ኢትዮጵያም በዓመት 40 ቢሊዮን ሜትር ኪዮብ ውሃ እንድትለቅ እንዲሁም የአስዋን ግድብ የውሃ መጠን ከምድር ወለል በላይ 165 ሜትር ላይ ሲደርስ የሕዳሴው ግድብ ዋና ሥራ ውሃ መልቀቅ ብቻ እንዲሆን ያቀረበችውን ምክረ ሀሳብ ኢትዮጵያ ውድቅ ማድረጓ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን የውጭ ጉዳይ እና የውሃ ሀብት ሚኒስትሮች የአሜሪካ የገንዘብ ሚኒስትርና የዓለም ባንክ ፕሬዚዳንት በተገኙበት ባደረጉት ውይይት ሦስቱ አገሮች በግድቡ ላይ የስምምነት ማዕቀፎችን ማስቀመጣቸው ይታወሳል።

ከስምምነት ማዕቀፎቹ ውስጥ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት ሥራ የወንዙ ተፋሰስ አገሮችንና የወንዙን ፍሰት ከግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ በየደረጃ እንዲሞላና የግድቡ ሙሌትም በክረምት ወራት እንዲሆን የሚለው ይገኝበታል።

ከዚህ ሌላ ግድቡ የመጀመሪያ ደረጃ ኤሌክትሪክ ሊያመነጭ የሚያስችለው ከባህር ጠለል በላይ 595 ሜትር ከፍታ ድረስ ውሃ መያዝ እንዲችልና በዚህ ጊዜ ግን አስከፊ ድርቅ ካጋጠመ ግብፅና ሱዳንን ታሳቢ ያደረገ እርምጃ እንዲወሰድ ብሎም የግድቡ ሙሌት የታችኞቹን ተፋሰስ አገሮች በማይጎዳ መልኩ መሆን እንዳለበት ተቀምጧል።

ኢትዮጵያም ግብጽና ሱዳንን ጨምሮ በታችኞቹ የወንዙ ተፋሰስ አገሮች ላይ ጉልህ ጉዳት በማያደርስ መልኩ ግድቡን ውሃ ለመሙላት እየተዘጋጀች መሆኑን በተደጋጋሚ ማሳወቋ ይታወሳል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም