የንግድ ህግን የማሻሻልና የመለወጡ ስራ እየተገባደደ መሆኑን ጠቅላይ ዐቃቢ ህግ ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የንግድ ህግን የማሻሻልና የመለወጡ ስራ እየተገባደደ መሆኑን ጠቅላይ ዐቃቢ ህግ ገለጸ
አዲስ አበባ ሰኔ 26/2010 የኢትዮጵያ ንግድ ህግን ለማጽደቅ የመጨረሻ ምዕራፍ መድረሱን ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ገለጸ። ህጉ ከ50 ዓመት በላይ የሚያገለግል መሆኑም ዛሬ በነበረው መድረክ ተገልጿል። የንግድ ህጉ አገሪቱ በኢኮኖሚው ዘርፍ የወሰደቻቸውን የቅርብ ጊዜ ለውጦችን መሰረት ያደረግና በቀጣይ የሚኖረውን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ታሳቢ በማድረግ መዘጋጀቱ ተነግሯል። በዘመናዊ የኢትዮጵያ ህግ ታሪክ ተጠቃሽ ከሆኑት የህግ መድብሎች መካከል አንዱ የሆነው የንግድ ህግ በስራ ላይ እንዲውል የተደረገው ከግማሽ ምዕተ ዓመት በፊት በ1952 ዓ.ም ነበር። ይሁን እንጂ የንግድ ህጉ በወቅቱ የነበረውን የአገሪቱን የንግድ እንቅስቃሴ መሰረት ያደረገና አሁን ካለው አገር አቀፍና ዓለም አቀፍ የንግድ እንቅሰቃሴ ለውጥ ጋር የሚጣጣም አይደለም። በዚህ መሰረት ለ58 ዓመታት ያገለገለውን የንግድ ህግ ሙሉ በሙሉ ለመለወጥ እየተሰራ ሲሆን የህጉ የአማርኛ ክፍል እየተጠናቀቀ መሆኑን ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ የህግ ጥናት ማርቀቅና ማስረጽ ዳይሬክተር አቶ በላይሁን ይርጋ ይናገራሉ። በመሆኑም አሁን ዓለም የደረሰችበትን የኢኮኖሚ ስርዓት ለውጥ መሰረት ያደረገ የንግድ ህግ በማስፈለጉ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ካለፉት ሁለት አመታት ጀምሮ የንግድ ህጉን ሲያረቅ መቆየቱን ተናግረዋል። አቃቤ ህጉ ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ ከምርምር ተቋማት፣ ከዩኒቨርሲቲዎች፣ ከመንግስት ተቋማትና ከሌሎች ጋር በመወያየት ለህጉ መሻሻል ግብዓት የሚሆኑ ሀሳቦች ተካተውበታል። በአሁኑ ሰዓት አጠቃላይ የንግድ ህጉን የማርቀቁ ጉዳይ በመጠናቀቅ ላይ መሆኑን ጠቅሰው ነጋዴዎና የንግድ መደብሮች፣ የንግድ ማህበራትና ኢንተርፕራይዝ፣ ስለ ባንክ ስራዎችና ተላላፊ የገንዘብ ሰነዶች፣ ስለ ኪሳራና የመጠበቂያ ስምምነቶች ዝርዝር ጉዳዮችን የያዘ መሆኑንም ዳይሬክተሩ ገልጸዋል። ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ህጉ ተጠናቆ እስኪጸድቅ ድረስ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመመካከር ሊካተቱና ሊሻሻሉ የሚገባቸው ጉዳዮች ላይ እየመከረ እንደሚቀጥል ተጠቅሷል።