በጋምቤላ ክልል የኮሮና ጥንቃቄ በማድረግ የእርሻ ሥራውን ለማከናወን ንቅናቄ ተጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
በጋምቤላ ክልል የኮሮና ጥንቃቄ በማድረግ የእርሻ ሥራውን ለማከናወን ንቅናቄ ተጀመረ
ጋምቤላ ኢዜአ ሚያዚያ 15 /2012 ዓም በጋምቤላ ክልል አርሶና ከፊል አርብቶ አደሩ እራሱን ከኮሮና ቫይረስ በመጠበቅ የእርሻ ሥራውን እንዲያከናውን ንቅናቄ መጀመሩን የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ ገለፀ ።
በክልሉ በመጪው የመኸር እርሻ ከ135 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ ሰብሎች ለማልማት ታቅዶ ወደ ትግበራ ምዕራፍ መገባቱንም ቢሮው ገልጿል።
የቢሮው ኃላፊ ዶክተር ሎው ኡቡፕ ለኢዜአ እንደገለጹት አርሶና ከፊል አርብቶ አደሩ በበሽታው ስጋት ከግብርና ልማቱ እንዳይዘናጋ በሁሉም አካባቢዎች የንቅናቄ ስራዎች እየተካሄደ ነው ብለዋል ።
በክልሉ ሁሉም ወረዳዎች አመራሮችንና ባለሙያዎችን በማሰማራት አርሶና ከፊል አርብቶ አደሩ ስለ በሽታው ግንዛቤ እንዲይዝ በማድረግ የእርሻ ሥራቸውን በአግባቡ እንዲያከናውኑ እየተደረገ ነው ።
በተለይም በማጃንግ ዞን ውጤታማ ስራዎች መከናወናቸውን ነው ዶክተር ሎው ኡቡፕ የገለፁት።
በክልሉ በምርት ዘመኑ ከ135 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ ሰብሎች በማልማት ከ3 ነጥብ 9 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ መታቀዱን ተናግረዋል።
በምርት ዘመኑ ለማልማት የታቀደው መሬት ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር በ11 ሺህ ሄክታር፤ ለመሰብሰብ የታቀደው ምርት መጠን ደግሞ በ700 ሺህ ኩንታል ብልጫ እንዳለው ገልጸዋል።
ቢሮው ለምርት ዘመኑ ከሶስት ሺህ ኩንታል በላይ የበቆሎ፣ የሩዝ፣ የለውዝና የማሽላ የምርጥ ዘር ግብዓት እያሰራጨ መሆኑም አስታውቀዋል።
በአሁኑ ወቅት የበልግ አብቃይ በሆነ የማጃንግ ዞን ቀድመው የሚዘሩ የበቆሎና የማሽላ ሰብሎች መዘራታቸው ጠቁመው በአኝዋሃና በኑዌር ዞኖችም ሰፊ የማሳ ዝግጅትና አልፎ አልፎ የዘር ሥራ መጀመሩንም ነው ኃላፊው የተናገሩት።
በማጃንግ ዞን በመንጌሽ ወረዳ የሾኔ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ዩኤል ኦዎን በሰጡት አስተያየት አካላዊ ርቀታቸውንና ንጽህናቸውን በመጠበቅ የኮሮና በሽታን መከላከል እንደሚችሉ በእምነት ተቋማትና በባለሙያዎች ግንዛቤ ማግኘታቸውን ተናግረዋል።
''በተሰጣቸው ግንዛቤ መሰረትም እራሳቻውን በመጠበቅ የእርሻ ስራቸውን በተገቢው ሁኔታ እያከናወኑ እንደሚገኙ ጠቁመው በአሁኑ ወቅት የበቆሎ ሰብል ዘርተው በቡቃያ ደረጃ ላይ ይገኛል ብለዋል።
የእርሻ ስራቸውን ከአንድ ወር በፊት ጀምሮ በአግባቡ እያከናወኑ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ የዚሁ ወረዳ የጎሽኔ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ገባቦ ጋኒቾ ናቸው።
የኮሮና በሽታ በመከላከል የእርሻ ስራቸውን በትኩረት እንደሚያከናውኑ ተናግረዋል።