በትግራይ ደቡባዊ ዞን የመብራት መቋረጥ በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ችግር አስከትሏል - ኢዜአ አማርኛ
በትግራይ ደቡባዊ ዞን የመብራት መቋረጥ በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ችግር አስከትሏል
ማይጨው ኢዜአ ሚያዚያ 15 ቀን 2012 ዓም.በትግራይ ደቡባዊ ዞን የመብራት አገልግሎት በመቋረጡ ምክንያት ለችግር መጋለጣቸውን የተለያዩ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ገለጹ።
በማይጨው ከተማ የሚገኘው የለምለም ካርል ሆስፒታል ስራ አስኪያጅ አቶ ገብረእግዝአብሄር ኪሮስ ለኢዜአ እንደገለጹት በመብራት መቋረጥ ምክንያት ሆስፒታሉ የቀዶ ህክምና አገልግሎት ለማቆም ተቃርቧል ።
ከኦክስጅን እርደታ ውጭ መቆየት የማይችሉ ታካሚዎች ችግር ውስጥ መውደቃቸውንም ተናግረዋል።
በሆስፒታሉ ለጊዜው ጀነሬተር በመጠቀም አገልግሎት እየሰጠን ቢሆንም የመብራት አገልግሎቱ ችግር በፍጥነት ካልተፈታ በዚህ ሁኔታ ረጅም ርቀት ሊጓዝ እንደማይቻል ገልጸዋል።
የማይጨው ከተማ የንጹህ መጠጥ ውሀ እቅርቦት ጽህፈት ቤት ስራ አስክያጅ አቶ ሀይለ ተሰማ በበኩላቸው በመብራት አገልግሎት መቋረጥ ምክንያት የንጹህ መጠጥ ውሀ አቅርቦቱ መስተጓጎሉን ገልፀዋል ።
ችግሩ አሁን ካለው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መከላከል ጋር ከባድ ያደረገው በመሆኑ ጊዜያዊ መፍትሄ ለመስጠት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
የማይጨው ከተማ ኤለክትሪክ አገልግሎት ማእከል ስራ አስኪያጅ አቶ አብዪ አሰፋ በበኩላቸው ችግር የተፈጠረው አላማጣ ከተማ የሚገኘው የሀይል ማስተላለፍያ ትራንስፎርመር በመቃጠሉ ምክንያት ነው ብለዋል ።
ይህንኑ ተከትሎ በትግራይና በአማራ ክልል የሚገኙ ከ15 በላይ ከተሞች የመብራት አገልግሎት ከተቋረጠባቸው ሁለት ቀናት እንደሆናቸው ተናግረዋል ።
በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የሰሜን ሪጅን መብራት አገልግሎት ዳሬክተር አቶ ሮቤል ገብረ እግዝአብሄር ስለ ጉዳዩ ተጠይቀው እንዳሉት ችግሩ የተፈጠረው አላማጣ ከተማ የሚገኘው የማከፋፈያ ትራንስፎርመር በመቃጠሉ ነው ብለዋል።
ችግሩን በጊዜያዊነት ለመፍታት ጥረት እየተደረገ በመሆኑ ዘላቂ መፍትሔ እስኪገኝ ድረስ በፈረቃም ቢሆን በአምስት ቀናት ውስጥ አገልግሎት የሚያገኙበት ሁኔታ እንደሚፈጠር ገልፀዋል ።